Friday, September 27, 2019
የሊዮ ሜሲ ወላጆች ልፋት
የሊዮ ሜሲ ወላጆች ልፋት
(ክፍል 8)
ውድ ተከታታዮቻችን ፅሁፉን ከጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ገፅ መዋሳችንን በቅድሚያ መግለፅ እንፈልጋለን።
ሊዮ የቀን ውሎውን ሲተርክለት ሆርጌ በሆቴል ክፍሉ ወንበር ላይ ተቀምጦ በተመስጦ አዳመጠው፡፡ ወደ ስፔን ከመምጣታቸው አስቀድሞ ስለባርሴሎና እግር ኳስ ክለብ ለትንሹ ልጅ አብጠርጥሮ ነግሮታል፡፡ አስተምሮታል ቢባል ይቀላል፡፡ ከተጫዋቾቹ ቁመት አንስቶ እስከሚለብሱት ማሊያ ቀለም፣ ምንም የቀረው ነገር የለም፡፡ በክፍሉ መሐል ወለል ላይ ቆሞ ስላጋጠሙት ልጆች ሲነግረው አባት ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ተገረመበት፡፡
‹‹ምን ዓይነት አስደናቂ ውሎ ነው ያሳለፍከው?›› ካለ በኋላ በወላጅ ፍቅር አቀፈው፡፡
‹‹ግን..›› አለ ሆርጌ የቀረው ነገር እንዳለ ለማስታወስ፡፡ ‹‹ግን እዚያ ድረስ መሄድህ ያልቀረ፣ ላ ማሲያን ውስጥ ውስጡን ሳታይ መምጣት አልነበረብህም፡፡ ማየት ነበረብህ›› አለው በቁጭት መልክ፡፡
ሊዮ መለሰለት፡፡
‹‹ግዴለም አባባ!.. ግዴለም!… አንድ ቀን ማየቴ አይቀርም! …አንድ ቀን!››
*
ሊዮ በብስጭት ልብሱን ወደ ሻንጣው ውስጥ እየወረወረ ‹‹እነዚህን ሰዎችኮ አላምናቸውም›› እያለ የመጨረሻውን ልባሽ ወደ ውስጥ ካስገባ በኋላ ሻንጣውን በኃይል ዘግቶ የጎኑን ዚፕ አንሸራቶ ጠረቀመው፡፡
‹‹ከእኛ ጋር ስምምነት ሊያደርጉ ያልፈለጉት ለምንድነው?›› አለ ሆርጌ ንዴት ቀላቅሎ፣ ወደ ሊዮ ጀርባ እየመጣ ጓዙን መሸከፉ ላይ ሊረዳው እየሞከረ፡፡
‹‹ማንም ቢሆን ከሁለት ሳምንት በላይ ሊታገስ አይችልም›› ካለ በኋላ አንዱን የውስጥ ሱሪውን ከፍ አድርጎ በአንክሮ ተመለከተው፡፡
‹‹እነዚህን ነገሮች ግን አጥበሃቸው ታውቃለህ?››
ሊዮ አንገቱን በአዎንታ ሲነቀንቅለት ሆርጌ የያዘውን ወርውሮ ወደ ሻንጣው ውስጥ አስገባው፡፡
የታዳጊው ሊዮኔል ሜሲ የባርሴሎና ነገር አልለየለትም፡፡ አባትና ልጅ ሃገራቸውን ጥለው መጥተው በሆቴል ከከተቱ ሁለት ሳምንት አልፏቸዋል፡፡ ግን የሊዮ ነገር ቁርጡ አልታወቀም፡፡ ሆርጌ በየዕለቱ ከባርሴሎና ስዎች ጋር እየተገናኘ ቢነጋገርም ተጠራጥሯቸዋል፡፡ በተለይ መልማዩ ጋስፐርን ሳያየው አይውልም፡፡ የታዳጊዎች ጉዳይ የሚመለከተው አሰልጣኝ ካርሌስ ሬክሳችን ነው፡፡ እርሱ ደግሞ ለኦሊምፒክስ ወደ አውስትራሊያ በመጓዙ እስኪመጣ መጠበቅ እንዳለበት ጋስፐር ይነግረዋል፡፡ እንደተነገራቸውም ቢጠብቁም ጠብ የሚል ነገር ጠፋ፡፡፡ አባትና ልጅ ትዕግስታቸው እየተሟጠጠ ሄደ፡፡
ውሳኔውን ለመስማት ቢዘገዩም ሆርጌ በሊዮ ብቃት ተማምኗል፡፡ ሙከራው ይሰጠው እንጂ ወደ ባርሴሎና ታዳጊ ቡድን የሚያስገባውን ፈተና አልፎ ውል እንደሚፈርም አይጠራጠርም፡፡ ሆኖም ቀናት አለፉ፡፡ ሬክሳችን የበላ ጅብ አልጮህ ሲል የሆርጌ ትዕግስት ጽዋ ሞልቶ ፈሰሰ፡፡
አባት ሲበሳጭ፣ ልጅ አብሮ ይበሳጫል፡፡ ሆርጌ እንዲህ ሲሆን ማየት ለሊዮ ደስታን የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ይልቅስ በባርሴሎና የመታቀፉ ነገር እውን ስለመሆኑ እንዲጠራጠር አደረገው፡፡ ለሊዮ አስፈላጊው ነገር ጨዋታ መጫወቱ ነው፡፡ የማይጫወት ከሆነ ግን እዚህ መቆየቱ ምንም ትርጉም የለውም፡፡
የሊዮ ሻንጣ ተዘጋጅቶ አበቃ፡፡ ሆርጌ ስልኩን አንስቶ ወደ ጋስፐር ደወለ፡፡ ጓዛቸውን መሸከፋቸውንና ወደ አርጀንቲና ሊመለሱ እንደተዘጋጁ አረዳው፡፡
‹‹ሚስተር ሜሲ እለምንሃለሁ›› አለ ጋስፐር በተማጽኖ፡፡
‹‹አንድ ቀን ብቻ ቆይ፡፡ ነገ በዕድሜ ትንሽ ከፍ ከሚሉ ልጆች ጋር ጨዋታ አዘጋጅተንለታል፡፡ ሚስተር ሬክሳችም ከኦሊምፒክሱ የተመለሰ በመሆኑ ሊዮን ሊመለከተው ቃል ገብቶልናል፡፡አንድ ቀን ብቻ!.. አንድ ተጨማሪ ቀን!...እባክህ!››
ይህን ሲሰማ ሆርጌ የስልኩን መነጋገሪያ በደረቱ ላይ ለጥፎ ጥቂት አፍታ በመውሰድ ሊዮን በአንክሮ ተመለከተው፡፡ ሊዮም ‹‹በዕይታ የመልስ ምት›› ምላሽ ሰጠው፡፡
‹‹እሺ ሲኞር ጋስፐር! ይሁን…፣ አንድ ቀን!››
በምልመላ ኃላፊው ሃሳብ ተስማማ፡፡
ሆርጌ የሊዮ ፊት እንደ ጠዋት ጮራ ሲበራ አየ፡፡ ስልኩን እንደዘጋ ልጅ አባቱ ላይ በደስታ ተጠመጠመበት፡፡ ‹‹አባዬ አመሰግናለሁ›› ካለ በኋላ ፊቱን ጭምቅ አድርጎ ከአባቱ ደረት ላይ አሳሳመው፡፡
‹‹ምንም ማመስገን አያስፈልግህም፡፡ እንደው ስታስበው ይህን የመሰለ ታላቅ እድል እንዲያመልጥህ የምፈቅድ ይመስልሃል?... ስማ ልጄ! አንዳንድ ጊዜ ጨዋታህን ጠንከር ማድረግ አለብህ፡፡››
ሊዮ እንደገና አባቱን አጥብቆ አቀፈው፡፡
ለሁለት ሳምንት ታግሶ ቢቆይም፣ ነገን ለማየት ቸኮለ፡፡ ነገ አልደርስ ብሎ ናፈቀው፡፡
*
በበነጋው፣ ሰዓቱ ሲደርስ ሊዮ ከሆቴሉ እስከ ካምፕ ኑ ድረስ የሄደው በሩጫ ነበር፡፡ ያቺ ቀን ሲጠባበቃት የነበረችው ቀን ናትና ቸኩሎባታል፡፡ ገና የሙከራ ጨዋታውን ሳይጫወት ወጣት ቡድኑን የሚቀላቀልባት ቀን አድርጎ አሰባት፡፡ ይህ ጨዋታ እጅግ በጣም ውድ ዋጋ ያለው ጨዋታ በመሆኑ ያለውን ሁሉ አውጥቶ የሚሰጥበት እንደሆነ አልጠፋውም፡፡ የሚመለከቱት እነማን እንደሆኑ ስለማይታወቅ አቅምን ሁሉ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ሊዮ ሲሮጥ ሆርጌ ግን ዘና እያለ ተራመደ፡፡ በሳቢኖ ደ አራና ጎዳና በሚያየው ሁሉ እየተዝናና፣ ጀነን ብሎ በራሱ እና ይህን ዕድል ባገኘው ልጁ ኩራት እየተሰማው ወደ ካምፕ ኑ አመራ፡፡ በዋናው ስታዲየም አቅራቢያ በሚገኘው ቁጥር-3 ትንሹ ሜዳ ሊዮ ይጫወት ዘንድ ፕሮግራም የተያዘለት ከ14 ዓመት ልጆች ጋር ነበር፡፡ ልክ 7፡00 ሰዓት ሲሆን ጨዋታው ይጀምራል ተብሏል፡፡
ሊዮ በመልበሻ ክፍሉ ሲደርስ ሌሎች ተጫዋቾች ራሳቸውን ለጨዋታው አዘጋጅተው ወደ ሳሩ ሜዳ ወጥተው አገኛቸው፡፡ አሰልጣኙም አርጀንቲናዊው መምጣቱን እንደተመለከተ ፈጥኖ ጠራው፡፡
‹‹ሊዮ ወዲህ ና! …ወዲህ!››
ከልጆቹ ተቀላቀለ፡፡ በዚያ ቀን በላ ማሲያ መግቢያ ደጃፍ ላይ ያስደነገጡት ታዳጊዎች አንድሬ ኢኒዬሽታ፣ ሴስክ ፋብሪጋዝና ቻቪ ሄርናንዴዝ ከመካከላቸው ነበሩ፡፡
‹‹ሁላችሁም ስሙኝ!›› አለ አሰልጣኙ፣ ሊዮን ከጨዋታው በፊት ሊያስተዋውቅ እጁን በትንሹ ልጅ ትከሻ ላይ አሳርፎ እየተዘጋጀ፡፡
‹‹አዲሱ አጥቂያችንን እወቁት፡፡ ሊዮ ሜሲ ይባላል፡፡››
ይህን ጊዜ ሁሉም አጨበጨበ፡፡ ሊዮ የሚያየውን ሁሉ ማመን አቃተው፡፡
(ይቀጥላል)
ምንጭ - የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ቴሌግራም ቻነል
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
"ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል
"ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል የፈረንሳዊው ኮከብ ፖል ፖግባ ወኪል የሆነው ሚኖ ራዮላ ፤ አማካዩ በክረምት የዝውውር መስኮት ወደ ቱሪን ሊመለ...

No comments:
Post a Comment