ሮናልዶ በመጀመሪያዋ ቀን (የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ማስታወሻዎች)
ውድ አናባቢዎች ፅሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ መሆኑን መግለጽ እንፈልጋለን
በክፍሉ ጥግ ላይ በዝምታ ተቀምጦ ከራሱ ጋር ይታገላል፡፡
ይታታላላቅ ተጫዋቾች መካከል ምን ሊያደርግ እንደመጣም አያውቀውም፡፡ እዚያ መገኘቱን ማመን አልቻለም፡፡ ዕድሉን ማግኘቱ አስገርሞታል፡፡ ተገርሞ፣ ተገርሞም አላበቃም፡፡ ሲሻው የኃላፊነት ስሜትም ሽው እያለ ይሰማዋል፡፡ የመጀመሪያ የልምምድ ፕሮግራም ነውና ማንነቱን አሳይቶ ያየው ሁሉ እንዲያስታውሰው ይሻል፡፡ ብቅ ብሎ ታይቶ መጥፋትንና መረሳትን አይፈልግም፡፡ ራሱን ሊያሳይ ቆርጧል፡፡ ከከዋክብቱ ጋር ወደ ልምምድ ሜዳ ሲገባ ልቡ ደረቱን በጥሶ ሊወጣ የፈለገ እስኪመስል ዘለለበት፡፡
*
…የታዳጊነቱ ዘመን አልፎ ጉርምስና ከተፍ ያለለት ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የእናቱ ነገር ሲያስጨንቀው ኖሯል፡፡ በተጫዋችነቱ ገንዘብ ማግኘት ሲጀምር የሆቴል ስራዋን እንደምታቆም፣ መኖሪያ ቤት የላትምና የቤት ባለቤት እንደሚያደርጋትም ቃል ገብቶላታል፡፡ ሆኖም የፕሮፌሽናልነት የመጀመሪያ ክፍያው እንዲያ ላለ ቅንጦት አልበቃውም፡፡ በወጣት ቡድን ተይዞ ወደ ሊዝበን ከተማ ከመጣ በኋላ ግን ክለቡ በኪራይ ወደሰጣቸው ቤት እንድትዛወር አደረገ፡፡ ቃሉን አክብሮ የራሷን ቤት እስኪገዛላት ድረስ ግን ጠንክሮ መስራትና ከፍ ያለ ክፍያን ማግኘት ነበረበት፡፡ አሁን ከትልልቆቹ ጋር የመለማመድ ዕድል ተገኝቷል፡፡ እንደዚያ ያለ ዕድል ደግሞ ካመለጠ ተመልሶ ላይመጣ ይችላል፡፡ ሰበብ ሳያበዙ መጠቀምን ይጠይቃል፡፡
በስፖርቲንግ ሊዝበን ላዝሎ ቦሎኚ በዋና አሰልጣኝነት ገና መሾሙ ነበር፡፡ ሮማኒያዊው በወጣት ቡድኑ ውስጥ ተስፈኛ ወጣቶችን ካየ አያልፍም፡፡ ከአዋቂዎቹ ጋር እንዲሰሩ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ሮናልዶም ሲጠራ ገና የ16 ዓመት ጎረምሳ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ልምምድ መውጣቱ ነው፡፡ በዚያች ቀን ጠዋት ትምህርት ቤት ውሎ ሲመለስ የወጣት ቡድኑ አሰልጣኝ ዦን ፖል ወደ ቢሮው እንዲመጣ አስጠራው፡፡
‹‹ራስህን አዘጋጅ፡፡ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ትሰራለህ›› ሲል በመልካም ዜና አስደነገጠው፡፡
ውሳኔውን ሲሰማ አይኑ ፈጠጠ፡፡ ለእናቱ መደወል ይፈቅድለት ዘንድ አሰልጣኙን ጠየቀው፡፡ ብዙ ሳያወራ የምስራቹን ለእናቱ ነገራት፡፡ ጊዜ ሳይወስድ ሮጥ ብሎ ወደ መልበሻ ቤቱ ሄዶ ታኬታውን ማዘጋጀት ጀመረ፡፡
ልምምዱ የሚጀመረው በ10፡30 ነበር፡፡ ገና የሁለት ሰዓት ጊዜ አለው፡፡ ሰዓቱ እየቆጠረ አንድ ሰዓት ተኩል ቀረው፡፡
…አንድ ሰዓት ቀረው፡፡
ከማንም በፊት ራሱን ለግዳጁ አዘጋጀ፡፡ ማሪዮ ጃርዴል፣ ጆአኦ ፒንቶ እና አንድሬ ክሩዝ እንዲሁ ተዘጋጁ፡፡
30 ደቂቃ ብቻ ቀረ…፡፡
በመልበሻ ቤቱ ከተጫዋቾች ጋር ከተቀላቀለ በኋላ ዙሪያው ያለውን ሁሉ በጥሞና ይመለከት ነበር፡፡ ትጥቆቻቸውን እንዴት እንደሚቀይሩ፣ የመጫወቻ ጫማዎቻቸውን እንዴት እንደሚጫሙ፣ ማን ከማን ጋር እንደሚነጋገር… ሁሉን እያየ ታዘበ፡፡
*
….. መጨነቁን ማወቁ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የሚያስፈልገውን ባያሟላ ኖሮ እዚህ ቦታ ከቶ እንዴት ሊመጣ ይችላል? እንዲሁ በባዶ ሜዳ ይህን የመሰለ ዕድል ያገኘ ማን አለ? ከጭንቀቱ ጎን ይህም ስሜት የልብ ልብ ይሰጠዋል፡፡
በልምምዱ ላይ የተለየ ነገር ማሳየት አልቻለም፡፡ ይህ ነው የሚባል ነገር ሳይሰራበት አለፈ፡፡ እንዲያውም የክሪስቲያኖ ውሎ መጥፎ ነበር፡፡ አልተሳካለትም፡፡ ማንም ከቁም ነገር አልቆጠረውም፡፡ ዞር ብሎ እንዲያዩት የሚያደርግ ጨዋታ አላሳየም፡፡ ስኬት በሯን አንቦራቃ ብትከፍትለትም አውቆበት ዘው ሊልበት አቃተው፡፡ አልሆነም፡፡
ከልምምዱ በኋላ አሰልጣኝ ቦሎኒ ክሪስቲያኖን የሚመለከተውን የምልመላ ሪፖርት አዘጋጀ፡፡
‹‹ቴክኒክ (ደካማ)፣ የአየር ላይ ኳስ (ደካማ)፣ ቴክኒክ (በቂ ስራ ያልተሰራበት)፣ የመከላከል ተሳትፎ (ደካማ)፣ አካላዊ ጉዳዮች (ደካማ)፣ የግልና የቡድን ታክቲክ (ግንዛቤ የሌለው)፣ በአእምሮ (ደካማ)፣ ለራሱ ብቻ የሚጫወት፣ የአእምሮ ጥንካሬ የሚጎድለው፣ ትኩረት የሌለው…›› የሚል ግምገማ ተጻፈበት፡፡ ብዙ ርቀት ለመጓዝ ያለመው ወጣት የማለዳ ፈተና በደካማ ውጤት ተጠናቀቀ፡፡
ሮናልዶ ግን ወድቆ አልወደቀም፡፡ ቁርጠኝነት አነሳው፡፡ ልፋት አጀገነው፡፡ ተሰጥኦው አስከበረው፡፡ ረጅሙን ርቀት በእንቅፋት ቢጀምርም አንድ ጊዜ መንገዱን ካገኘ በኋላ የሚያቆመው ጠፋ፡፡ ከሶስት እና አራት ወራት በኋላ ሁሉ ነገር ተገጣጠመለት፡፡ የብቃት ጸሐይ ከጣሪያ በላይ ሳይደርስ ላትጠልቅ ፊቷን አበራችለት፡፡ ጭንቀቱ በእርጋታ ተተካ፡፡ በስጋቱ ቦታ ድፍረት ቦታውን ያዘለት፡፡ የኳስ ፍርሃቱ እንደጠዋት ጤዛ ተነነ፡፡ ጭራሹኑ አንጋፋ ተጫዋቾች ላይ ናይለን ሊያስገባ ይሞክር ዳዳው፡፡ ሶምብሬሮ የእርሱ ትዕይንት፣ ድሪብሊንግ አመሉ ሆኑ፡፡ ጭራሹኑ በአንድ ትልቅ ተጫዋች ላይ የገባው ከባድ ሸርተቴ ተግሳጽ አስከተለበት፡፡
‹‹ትንሹ ልጅ ተረጋጋ! ተረጋጋ!›› የቁጣ ጩኽት ተከተለው፡፡
የክሪስቲያኖ ምላሽ ግን አስደናቂ ነበር፡፡
‹‹ቆይ!... የዓለም ኮከብ ተጫዋች ስሆን ይህን አነጋገር ትደግመዋለህ!›› እያለ ተዛበተባቸው፡፡
በወጣት ቡድኑ ጨዋታዎች ላይ ተዓምር ሲያሳይ የነበረው የማዴይራው ልጅ ሮናልዶ በዋናው ቡድን ልምምዶች ላይ ከብቃቱ ጋር ተመልሶ መጣ፡፡ ግን የጨዋታ ዕድል አልሰጡትም፡፡ የአንድ ዓመት ተኩል ታላቁ ሪካርዶ ኳሬዝማ እና በሁለት ዓመት የሚበልጠው ሂጎ ቪያና በተቀዳሚነት ለአዋቂዎቹ ቡድን ተጫወቱ፡፡ ከሲዝኑ አጋማሽ ወዲህ በመጫወት ውጤታማ የነበረው የስፖርቲንግ ሲዝን ቁልፍ አካላት ሆኑ፡፡ ሮናልዶ እንዲያጫውቱት አሰልጣኞቹን መወትወቱን ቀጠለበት፡፡ ክሪስቲያኖ ቸኩሏል፡፡ ቦሎኒ ግን ገና ነበር፡፡….
…በወጣት ቡድኑ ጨዋታዎች ላይ ተዓምር ሲያሳይ የነበረው የማዴይራው ልጅ ሮናልዶ በዋናው ቡድን ልምምዶች ላይ ከብቃቱ ጋር ተመልሶ መጣ፡፡ ግን የጨዋታ ዕድል አልሰጡትም፡፡ የአንድ ዓመት ተኩል ታላቁ ሪካርዶ ኳሬዝማ እና በሁለት ዓመት የሚበልጠው ሂጎ ቪያና በተቀዳሚነት ለአዋቂዎቹ ቡድን ተጫወቱ፡፡ ከሲዝኑ አጋማሽ ወዲህ በመጫወት ውጤታማ የነበረው የስፖርቲንግ ሲዝን ቁልፍ አካላት ሆኑ፡፡ ሮናልዶ እንዲያጫውቱት አሰልጣኞቹን መወትወቱን ቀጠለበት፡፡ ክሪስቲያኖ ቸኩሏል፡፡ ቦሎኒ ግን ገና ነበር፡፡
*
በኳስ የሁሉንም አፍ በግርምት እስኪያሲዝ ድረስ ሮናልዳ በሊዝበን በፈተና ውስጥ አልፏል፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ተማሪዎች በልዩ ዕይታ ይመለከቱት ጀመር፡፡ ክሪስቲያኖ ፖርቱጊዝን በሌሎቹ ቅላጼ አይናገረውም፡፡ በተለይ የመጀመሪያው ቀን የትምህርት ቤት ውሎ አስቀያሚ ሆነበት፡፡ ከልምምድ ማዕከሉ ወደ ትምህርት ቤቱ ለብቻው መሄድ ነበረበት፡፡ በታልሄሪያስ ሰፈር ይገኝ የነበረው ትምህርት ቤት አድራሻው ጠፍቶት ሲባዝን ቆይቶ ዘግይቶ ደረሰ፡፡ ስም ሲጠራ ‹‹አቤት!›› የሚል ጠፋ፡፡ በክፍሉ የተማሪዎች ዝርዝር ላይ የክሪስቲያኖ ቁጥር ‹‹አምስት›› ነበር፡፡ ስሙ ሲጠራ እጅ ማውጣትና ‹‹አለሁ በክፍሌ!›› የማለት ግዴታ አለበት፡፡ እና ቃል ሲወጣው በክፍሉ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በቅላጼው ይስቁበታል፡፡ ሲሳቅበት በፍርሃት ሰውነቱ በላብ ይጠመቃል፡፡ ምቾት ስለማይሰማው በክፍል መቆየቱን አይፈልገውም፡፡
ሰዎች በአነጋገሩ ለምን እንደሚስቁ ክሪስቲያኖ አይገባውም፡፡ ስላቁ ስሜቱን ይጎዳዋል፡፡ ያስለቅሰዋል፡፡ ብዙ ያለቅሳል፡፡ ትምርህት ቤቱ ያስጠላዋል፡፡ ወደ ቤቱ ሂድ ሂድ ይለዋል፡፡ እናቱ ግን ለክፍሉ ልጆች ትኩረት እንዳይሰጣቸውና ደንታ ቢስ እንዲሆን ትመክረዋለች፡፡ እርሱ ግን ችላ ሊላቸው አልቻለም፡፡ የሮናልዶ የማለዳ የእግር ኳስ ህይወት የመጀመሪያው ቀውስ ይኼው ነበር፡፡
በትምህርቱ ግልጽ ድክመት ይታይበት ነበር፡፡ በትውልድ ከተማው ፉንቻል ሳለ ሁለት ኮርሶችን ደግሟል፡፡ ወደ ዋና ከተማዋ የመጣበት የመጀመሪያ ዓመት እንዲሁ አልሆነለትም፡፡ የቀለም ትምህርት ላይ ስንፍና አለበት፡፡ የሊዝበንን ህይወት ለመልመድ ተቸገረ፡፡ ስፖርቲንግ በሶስት የተለያዩ ጊዜያት ሊያሰናብተው ወስኖ ነበር፡፡ ካለመልመድ የተነሳ የሚያሳየው አስቸጋሪ ባህሪይ ብቻ ሳይሆን ለትምህርት የሚሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ መሆኑ አሳሰበ፡፡ ራሱ ሮናልዶ ‹‹አሁንስ ይበቃኛል›› ያለበት ጊዜ ነበር፡፡ ቢሆንም በክለቡና በተጫዋቹ መካከል ስምምነት ላይ ተደርሶ ከታህሳስ 1997 እስከ ጃንዋሪ 1998 ድረስ ወደ ትውልድ ከተማው እንዲመለስ ተደረገ፡፡ ነገር ግን እዚያም በሌላ ኮርስ ከመውደቅ አልዳነም፡፡
ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ወደ ትምህርት ቤት ቢመለስም በሁለት ወይም ሶስት ዓመት ከሚበልጣቸው ልጆች ጋር ይማር ነበር፡፡ ዕድሜው 17 ዓመት ሲሞላ ግን ለክለብና ለብሔራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታዎች ላይ ይሳተፍ ስለነበር የቀለም ትምህርት ጊዜውን ይበልጥ አጠበበበት፡፡ በ2000-01 ዘጠነኛ ክፍል ሳለ በሰባት የትምህርት ዓይነቶች ወደቀ፡፡ በጨዋታዎች መብዛት ምክንያት በትምህርት ገበታው ላይ የተገኘው በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ብቻ በመሆኑ የ10ኛ ክፍል ሪፖርቱ የተሟላ ሳይሆን ቀረ፡፡
በአነጋገሩ ዘዬ የሚያሾፉበት የሊዝበን ታዳጊዎች በእግር ኳስ ችሎታው ሲያስደንቃቸው ተረቡ ቀስ በቀስ እየከሰመና ለእርሱ የሚሰጡት ክብር እየበለጠ ሄደ፡፡ ክሪስቲያኖ ጭራሹኑ በሌሎች ተማሪዎች ወይም ሰልጣኞች ላይ ይሳለቅ፣ ቀልድ አዋቂ ማንነቱ ብቅ ማለት ጀመረ፡፡
አባቱ ግን በልጁ የእግር ኳስ ብቃት ይኮራል፡፡ በሜዳ ላይ የሚያሳየውን አስደናቂ ትዕይንት አስመልክተው የተጻፉ የጋዜጣ ዘገባዎችን እየቆራረጠ ሰብስቦ ወደ ትውልድ ከተማው በመውሰድ በመጠጥ ቤቶች ለጓደኞቹ በኩራት ያሳያል፡፡
ሮናልዶ በእግር ኳሱ ቢኮራበት ሲያንሰው ነው፡፡ ልጁ ይፈጋል፡፡ ትጋት ባህሪዩ ነው፡፡ በወቅቱ ዝነኛ ተጫዋች እንደ ነበረው ቲዬሪ ሆንሪ ‹‹ፈጣን መሆን እችላለሁ›› በማለት ለብቻው የፍጥነት ልምምድ ይሰራ ነበር፡፡ ጓደኞቹ ምን እንደሚሰራ ሲጠይቁት ‹‹ሁለት ሳምንት ብቻ ስጡኝና እንደ ሆንሪ ፈጣን እሆናለሁ›› እያለ ይወራረዳቸዋል፡፡ በስፖርቲንግ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ አንድሬ ክሩዝ የተባለ ባለሰፊ ጡንቻ ብራዚላዊ ነበር፡፡ አንድ ቀን 90 እና 95 ኪሎግራም ሲያነሳ ክሪስቲያኖ አየው፡፡ ‹‹ቆይ ታያላችሁ 90 ኪሎ ማንሳት ባልችል›› እያለ በጓደኞቹ ፊት ሲዝት ቆይቶ በመጨረሻ ከጠንካራ ትጋት በኋላ ክብደቱን ማንሳት ቻለ፡፡
በየዕለቱ በመኝታ ክፍሉ አካላዊ ስፖርቶችን ይሰራል፡፡ በሳምንት ለሁለት ወይም ለሶስት ጊዜ ሌሊት ተነስቶ ድምጽ ሳያሰማ ወደ ጂምናዚየም ይሄዳል፡፡ ለብቻው ይሄዳል ወይም ሁለት ጓደኞቹን ይዞ ሌሊት ይወጣል፡፡ በእርሱ መሪነት ጂምናዚየው የሚገኝበትን ጊቢ አጥር ዘለው በጣሪያው ላይ ተንጠላጥለው በመስኮቱ በኩል ገብተው አካላቸውን ያጎለብታሉ፡፡ ተክለ ሰውነቴ ቀጫጫ ነው ብሎ ያምን ስለነበር ክብደት ያነሳል፣ በማሽን ላይ ብዙ ይሮጣል፡፡ ወደ ጂም እንዳይሄድ ሲሉ የአካዳሚ ጓደኞቹ ለበሮች ሌሎች ቁልፎችን እስከማበጀት ደርሰዋል፡፡ ለዕረፍት ወደ ማዴይራ ሲሄድ እንኳን፣ በማለዳ ተነስቶ ይለፋል፡፡ እንደ ጎረምሳ ጓደኞቹ አልኮል በደረሰበት አይደርስም፡፡ በቁርጭምጭሚቱ ላይ ክብደት እያሰረ ይሮጣል፡፡ ይለፋል፣ መጫወት፣ መለማመድ፣ መጫወት፣ አካልን ማዘጋጀት፣ ፉትቦል፣ ፉትቦል፣ ፉትቦል…. የሮናልዶ የጉርምስና ወቅት የዘወትር ልማድ ነበር፡፡
*
የስፖርቲንግ ዋና አሰልጣኝ ቦሎኒ በክሪስቲያኖ ውስጥ ታላቅ ተጫዋች ቢመለከትም ገና ብዙ ስራ ሊሰራበት እንደሚገባ አምኗል፡፡ ከ17 ዓመት በታች አሰልጣኙ ጆአኦ ኩቶ ጋር በመጣመር ለወጣቱ ልዩ ‹‹የብቻ›› የልምምድ ፕሮግራም አዘጋጁለት፡፡ በሳምንት ሁለት ጊዜ በወጣት ቡድኑ ወይም በአዋቂዎች ቡድን ውስጥ የሚሰሩ የጡንቻ ማጎልበቻ ልምምዶች ነበሩ፡፡ ልምምዶቹ በአግባቡ ከተሰሩ ጉዳትን ለመከላከል እና ከአዋቂዎች ጋር ለመጫወት ለሚያስችል አካላዊ ዝግጁነት ያደርሳሉ፡፡ የሮናልዶ የስራ ትጋት ግን አሰልጣኞቹን እስከማጭበርበር ድረስ አበቃው፡፡ በወጣት ቡድኑ የሰራውን በመደበቅ ከቦሎኒ ጋር ደግሞ ይለማመዳል፡፡ በዋናው ቡድን ውስጥ የሰራውን በመካድ እንደገና በወጣት ቡድኑ ውስጥ ጨምሮ ይለፋል፡፡ የሮናልዶ ግብ በእጥፍ ሰርቶም ቢሆን ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ብቻ ነበር፡፡ አሰልጣኞቹ ከመጠን በላይ ልምምድ እንዳይበዛበት ይጠነቀቁለታል፡፡ እርሱ ግን እየዋሻቸው ድርብ ስልጠና በመውሰድ ህልሙን እውን ለማድረግ ከአቅሙ በላይ ይተጋል፡፡
በዚያ ሰዓት ከአዋቂዎቹ ጋር ልምምድ ይስራ እንጂ ለዋናው ቡድን ገና አልተጫወተም፡፡ ለአሰልጣኞቹ ለምን እንደማያጫውቱት እየጠየቃቸው ዕድል እንዲሰጡት ዘወትር ይወተውታቸዋል፡፡ በመጀመሪያው ዓመት በቦሎኒ መሪነት ስፖርቲንግ ሶስት ዋንጫ አሸነፈ፡፡ ዘመኑ በታላቅ ስኬት ከተጠናቀቀ በኋላ ባለው የዕረፍት ጊዜ ክለቡ ቡድኑን ለማጠናከር ምን ያህል በጀት እንደመደበ አሰልጣኙ ለክለቡ ባለስልጣናት ጥያቄ አቀረበ፡፡ የበላዮቹ መልስ ግን ‹‹ምንም›› የሚል ሆነ፡፡
ምንም? እንዴት ምንም? በጀት የለም ማለት ነው፡፡
ምንጭ፦የመንሱር አብዱልቀኒ ቴሌግራም ቻነል
No comments:
Post a Comment