የሶልሻየር የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ (የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ማስታወሻዎች)
ፅሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው
ማሪዮት ሆቴል ድግስ ተዘጋጀልን። ሌሊቱን ከቤተሰቦቻችን ጋር በደስታ ዘለልን።
የኤፍ ኤ ካፕን ባሸነፍንበት ምሽት ግን ለደስታችን ገደብ አበጀንለት። ከስኮልስና
ሮይ ኪን በስተቀር ሌሎቻችን አልኮል እንኳን አልቀመስንም። የዋንጫ አሸናፊነቱ
ደስታ ቢኖርም ገና የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ከፊታችን አለና ተልዕኳችን
አልተጠናቀቀም።
በማግስቱ ወደ ባርሴሎና ከተማ በኮንኮርድ በረርን። ከማንቸስተር እስከ
ባርሴሎና ያለው አጭር ርቀት ሱፐር ሶኒክ በረራን አይፈልግም። ነገር ግን ዕድሉ
በየሳምንቱ የሚገኝ አይደለም። የአውሮፓ የክለቦች ዋንጫ ፍፃሜ በመሆኑ
ከመደበኛው የተለየ በረራ ይገባዋል።
የጫንነው የሻንጣ ብዛት ሲታይ የባርሴሎና ቆይታችን የዓመት ይመስል ነበር።
ጓዛችንን ሸክፈን ባርሴሎና ከተምን። እዚያም ስለፍፃሜው የምንወያይበት ሰፊ
ጊዜ አገኘን። ሰኞ ምሽት በሆቴላችን የመስኮት በረንዳ ላይ እኔ፣ ፊል፣ ኒኪ በት፣
ዴቪድ ቤካምና ስኮልስ ይህ ዕድል እንደገና ይመጣ ይሆን? በሚል መከርን።
ለአውሮፓ ፍፃሜ መድረሳችን ብቻ ሳይሆን አንድም የእንግሊዝ ክለብ ከ1985
ወዲህ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ አለማወቁ አጋጣሚውን ልዩ ያደርገዋል። የኑ
ካምፑ ጨዋታ ከቀናን ዘመኑን በሶስት ዋንጫ አሸናፊነት ክብር አጠናቀቅን
ማለት ነው። ይህንንስ ታሪክ ከጥቂቶች በቀር ማን ሰራው? እናም በእነዚያ ቀናት
በሚያስጨንቅ ደስታ ተወጥረን ከረምን።
አሰልጣኙን ከልብ የሚያሳስብ ጉዳይ አለ። ልባሙ ጓዳችን ሮይ ኪን እና
ፕሌይሜከራችን ስኮልስ አይሰለፉም። ተተኪዎች ተዘጋጅተዋል። ኒኪ ወደ መሐል
ይገባል። ቤካምም በዚያው ቦታ ሊያጣምረው ያስፈልጋል። ሪያን ጊግስና ዬስፐር
ብሎምክቪስት ደግሞ ለክንፎቹ አሉ። ለቀኙ ክንፍ፣ ምንም እንኳን ከዚህ በፊት
ተጫውቶበት ባያውቅም፣ ሌላው ምርጫ ኦሌ ጉነር ሶልሻየር ተጠባባቂ መሆን
ችሏል።
እውነት ለመናገር፣ የቡድኑ ቅርፅ አመርቂ አልነበረም። ግን ምን ይደረግ?
አሰልጣኙ ተገደደ። በሌሎችም ምክንያቶች ቢሆን ከባየርን ሙኒክ ጋር የነበረን
ጨዋታ በብዙ የተዳከምንበት ነበር። እኔም ብሆን ብሽሽቴ ምቾት ነስቶኛል።
ይመዘምዘኝ ይዟል። ብዙ የማፈትለክ ሩጫዎችን ስንሮጥ ከርመናል። ቢሆንም…፣
ቢሆንም… ያለ ሁለቱ ቁልፍ ተጫዋቾቻችን አንድ የመጨረሻ ጨዋታን ብቻ
ማሸነፋችን እጅግ አስፈላጊው ተልዕኳችን ነበር።
……በኑ ካምፕ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 20 ደቂቃ ሲቀረው ቀና ብዬ ደጋፊዎቻችንን
ተመለከትኳቸው። 1ለ0 እየተመራን ነው። "የሚጨፍሩበት አንድ ነገር
ሳናበረክትላቸውማ ወደ ሃገራችን መመለስ የለብንም" ስል አሰብኩ። በዚያ ሰዓት
ደጋፊዎቻችን ዝማሬያቸውን አቁመዋል። ባየርን አልተቻለም። ይታገላሉ፣ ያጠቃሉ፣
የግቡ ቋሚ ብረት ይመልስባቸዋል፣ ጎል እንዳያስቆጥሩ አግዳሚው
ያግዳቸዋል። የእኛ ነገር ያበቃለት ይመስል ነበር።
ዕረፍት ሰዓት ላይ አሰልጣኙ ንግግር አደረገልን። አሌክስ ፈርጉሰን ከተሸነፍን
ዋንጫውን ማንሳት ቀርቶ፣ መንካት እንኳን እንደማንችል አስረግጦ አስታወሰን።
በሽንፈት ስሜት ከዋንጫው ጎን ስለማለፍ አስቀያሚ ህመም ነገረን። ለትግል
የሚያነሳሳ ዲስኩር አደመጥን።
ከምክሩም በላይ ግን ትክክለኛው የተጫዋቾች ቅያሬ በዚያ ጨዋታ ዕጣ
ፈንታችን ለመቀየሩ ዓብይ ምክንያት ነበር። ብሎምክቪስት ወጥቶ ቴዲ
ሼሪንግሃም ወደ ሜዳ ገባ። ቅያሪው ጊግስን ወደ ቦታው፣ ወደ ግራ ክንፍ
መለሰው። ቤካም ደግሞ የእርሱ ወደ ሆነው ቀኝ ክንፍ መጣ።
ድዋይት ዮርክ ደግሞ ከአጥቂ ጀርባ ወዳለው ቦታ መለስ አለ። ከዚህ በኋላ
ባልታሰበ ፍጥነት ማርሻችንን ቀየርን። የመስመር ተከላካዮችም በጨዋታው
ለመጀመሪያ ጊዜ ተደርበን በመውጣት ማጥቃት ጀመርን።
ሁኔታው ሁሉ አዲስ የሆነበት ባየርን ይሄኔ ብርክ ያዘው።
አንዲ ኮል ተቀይሮ ሜዳውን ለቀቀ። ሶልሻየር ተካው። የተቀያሪዎቹ ያልደከሙ
እግሮች ሩጫቸውን አጠናከሩ። የተቀረነውም ብርታትን አገኘን። ተነሳሳን።
አራተኛው ዳኛ የሰዓት ሰሌዳውን ሲያወጣ አየሁት። ሶስት ደቂቃ ተጨመረ።
በክንፍ ኮሪደር ላይ የምበርበት አቅም ዘግይቶ መጥቶልኛል። በዓመቱ መጀመሪያ
ላይ ከነበረን ጉልበት ያልተናነሰን ኃይል ተላበስን። በተቻኮለ ማጥቃት ጫናችንን
ጨመርን።
…የሼሪንግሃም ጎል ተቆጠረ። ውጤት 1- 1።
ሰዓቱ አለቀ ሲባል ኦሌ ሌላ ጎል ደገመ። መላው የቡድኑ አባላት ወደ እርሱ
ሮጡ። በጉልበቶቹ ተንሸራቶ ወደ ደጋፊዎች ሲጠጋ እኔን አንዳች ነገር ጎትቶ ወደ
ኋላ አስቀረኝ። ከመሃል ሜዳው መስመርም ማለፍ ሳልችል በነበርኩበት ቀረሁ።
የደስታ ስሜት አሰከረኝ። ለራሴ ተደስትኩ፣ ለክለቤ ተደሰትኩ፣ ለደጋፊዎቻችን
ተደሰትኩ፣ ለኦሌ ተደሰትኩ። ለ11 ዓመታት በመልበሻ ቤት ከኦሌ ጎን
ተቀምጫለሁ። በአንድ በኩል ኦሌ፣ በሌላ በኩል ስኮልስ አጅበውኛል። ኦሌ ምን
አይነት ድንቅ ሰው መሰላችሁ! ራስ ወዳድ ያልሆነ፣ ከጎል አስቆጣሪዎች በተለየ
ለቡድን ጥቅም የሚሰራ ተጫዋች መሆኑን እመሰክራለሁ። ያ የክብር ታሪክ
ከምርጦቹ አንዱ ለሆነው ኦሌ የሚገባው ነበር።
"Oh My God! We've Done It!"
ከዚያ ወዲህ ደግሜ ደጋግሜ የጨዋታውን ሃይላይት ተመልክቻለሁ። ዛሬ ላይ
ሆኜ ከፈንጠዚያው ምን ያህሉን እንደማስታውስ እርግጠኛ አይደለሁም። …
የባየርን ተከላካይ ሳሚ ኩፎር ቤቱ ተዘርፎ ኦና እንዳገኘው ሰው በንዴትና ቁጭት
ተብከንክኖ ወዲያ ወዲህ ሲራወጥ ይታየኛል።… ዴቪድ ሜይ በዋንጫው
ፖዲየም ላይ ከሁሉ ከፍ ብሎ ሲንጠላጠል በአይነ ህሊናዬ ይመጣል።… መላው
የቡድኑ አባላት በሜዳው መሐል ተሰብስበን "ሲት ዳውን" የሚለውን ዘፈን
ስንዘምር ይታወሰኛል።… ኪን እና ስኮልስ ዋንጫውን ጨብጠው ከክብር ጋር
የሚያልፉበትን ኮሪደር ሰርተን ስናጅባቸው ትዝ ይለኛል።
ያ ክብር ይለያል። 3-0 አሸንፈን ቢሆን ኖሮ ማን እንዲህ ያስታውሰዋል?
ደስታችንም ከተለመደው ደስታ በምንም ባልተለየ ነበር።
እንቅልፍ እንዳልነበረን ያለብዥታ አስታውሳለሁ። የባርሴሎና ፀሐይ ዘግይታ ወደ
አድማሱ ስትገባ አይረሳኝም። ማንም ያ ምሽት እንዲነጋ አይፈልግም ነበር።
ማንስ ልተኛ ብሎ ወደ መኝታው ይሄዳል? እንቅልፍ አይናፈቅም። እረፍት
አይታሰብም። ድሉ ተራ ድል አልነበረምና። በብዙ ትግልና የመጨረሻ ሰዓት
ውጥረት የተፃፈ የስፖርቱ ዓለም ልብ አንጠልጣይ ድራማ ነበር እንጂ።…"
………
(ከጋሪ ኔቪል ግለ ታሪክ መፅሐፍ ላይ ተወስዶ በአጭሩ የቀረበ፣ የማንቸስተር
ዩናይትድ የ1998/99 የሶስትዮሽ ዋንጫ አሸናፊነት ታሪክ)
No comments:
Post a Comment