ያበደው የአጉዌሮ ቀን (የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ማስታወሻዎች)
ፅሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው
አልጃዚራ እንኳን "አልቋል" ብሎ ደምድሞታል። "ሲቲ አቻ በመለያየቱ ማንቸስተር
ዩናይትድ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የእንግሊዝ ሻምፒዮን ይባላል" ሲል
በስፖርት ዜና ሰዓቱ ላይ አወጀ። "ሁሉ አበቃ" ብሎም የዕለቱን ውጤቶች ዝርዝር
በስክሪኑ ላይ አሳየ። የሲቲና ኪውፒአር ጨዋታ ውጤት 2ለ2 ተብሎ
ተመዝግቧል። ከጎኑ ጨዋታው ገና እንዳላለቀ የሚያመለክት ምንም ጠቋሚ
ነገር አልነበረም።
በኤቲሃድ መደበኛው 90 ደቂቃው ተጠናቆ አምስት የባከኑ ደቂቃዎች ተጨመሩ።
ውጤት 2ለ2። በዚሁ ካበቃ ዩናይትድ የሊጉን ክብር ዘውድ ይደፋል። ሲቲ
ለመጨረሻዋ ፍልሚያ ቆረጠ።
ሜይ 13 ቀን 2012።
* * *
"ሰዓቱ 95 ደቂቃ መሙላቱን ስመለከት አሁን ካላስቆጠርን ያበቃለታል አልኩኝ።
የእጅ ውርወራ አገኘን። ኳሷ በቀስታ ወደ ሜዳው መጣች። አርዝሞ በመላክ
ማፋጠን ቢቻልም ውጤታማ ላደረገን መርሃችን ታማኞች መሆን ነበረብን።
ወደኋላ ጠለቅ ብዬ በመሳብ ከናይጀል ዴ ዮንግ ኳስ ለመቀበል ራሴን አዘጋጀሁ።
ከዚያም ለማሪዮ ባሎቴሊ ሰጠሁትና በድጋሚ ልቀበለው ወደ ፍፁም ቅጣት ምት
ክልሉ ሮጥኩ።
ባይመቸውም፣ ወድቆ እግሩን በመሬቱ ላይ ጎትቶ ኳሷን ወደ እኔ ገፋ አደረጋት።
ስመኘው የነበረውን ብቸኛ አጋጣሚ አገኘሁት። ባለ በሌለ አቅሜ አጠንክሬ
መታኋት።
ኳሷ መረቡን ስትነቀንቀው አስታውሳለሁ። ጆሮ የሚያደነቁር ጩኸት ተከተለ።
ከዚያ በኋላ የሆነው ሁሉ በሰመመን የማየው ሆነ።
ማሊያዬን አውልቄ በአናቴ ላይ እያሽረከርኩት ሮጥኩ። እብደት መጣ። ራሴን
ረሳሁ። ሰዓቱ እንዳበቃ ስላየሁ ጎሏ የዋንጫው ባለቤት እንደምታደርገን
አውቃለሁ። ግን ድንግዝግዙ ተከተለኝ። ጓደኞቼ በደስታ አሯሩጠው ከመሬት
ከደባለቁኝ በኋላ እንደሚወዱኝ ሲነግሩኝ በከፊል ታወቀኝ። ባሎቴሊ ጎትቶኝ
"አንተ የተረገምክ! እንዴትባህ እንደምወድህ ታውቃለህ?" አለኝ።
ከጎሉ በኋላ ጨዋታው ከመሐል ሜዳ ሲጀመር አላስታውስም። የሚታዩኝ በደስታ
የከነፉ ሰዎች ብቻ ናቸው።
ስለጨዋታው መጀመር ከቶ ማን ሊያስብ ይችላል? ሰዎች ወደ ሜዳው ሲገቡ
ይታዩኛል። ግን ሁሉም በደመነፍስ ነው። የሲቲ ደጋፊዎች ያቅፉኛል። "I Love
You!" ይሉኛል። ያመሰግኑኛል። በቅጡ አልሰማቸውም። እኔ ራሴን አይደለሁም፣
አንዳች አፍዝ አደንግዝ ይዞኛል።
ዞር ብዬ ሳስታውሰው ፍፁም እብደት ነበር። ያን ከመሰለ ጎል በኋላ ማበድ
ላያስገርም ይችላል። የእኔ ግን ከልክ ያለፈ፣ የለየለት ነበር።
በመልበሻ ቤት ከባድ ድካም ተጫነኝ። ቁጭ ብዬ ሃሳቤን ለመሰብሰብ ፈለግኩ።
ግን አልቻልኩም። እንዴት ይቻላል? ፈንጠዚያው ገና መጀመሩ ነበር። ቢራና
ሻምፓኝ ተራጨን። ከዋንጫው ጋር ፎቶዎች ተነሳን።
ከታጠብኩ በኋላ ልብሴን ቀየርኩ። ስልኬን ሳበራ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፅሁፍ
መልዕክቶች ደረሱኝ። የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች፣ ከግብ ጠባቂ
እስከ አጥቂ ድረስ፣ አንድም ሳይቀሩ የደስታ መግለጫ ልከውልኛል።
ለመልዕክቶቹ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሶስት ቀን ፈጀብኝ።
ቤተሰቦቼን ሳገኝ ሁሉም ተደስቷል። ግን የእኔ ድንዛዜ አልለቀቀኝምና ምን
እየተደረገ እንደሆነ አስረግጬ መረዳት አቃተኝ። ቤተሰቦቻችን በተገኙበት መላ
የቡድኑ አባላት ለራት ግብዣ ማዕድ ቀረብን። አልኮል የማትጠጣዋ እናቴ
ጨርቋን ጥላ አንድ መለኪያ ስትገለብጥ አየኋት። ምሽቱን ሁሉ በደስታ
ተፍለቅልቃ ስታወራ፣ ስትጫወት አመሸች። አባቴም እንዲሁ ቦረቀ።
ወደ ቤት የሄድነው በሚኒባስ ነበር። በጉዞ ላይ ሁሉም ይዘፍናል። ይደሰታል። እኔ
ግን ያው ነኝ። ፍዘቱ አልለቀቀኝም። ከሌሎች በመንፈስ ተነጥያለሁ። "ይኼ ሁሉ
የሚሆነው ለምንድነው? እንዲህ የሚሆኑትስ ለምን ይሆን?" እያልኩ ራሴን
እጠይቅ ነበር።
ከመተኛቴ በፊት በላፕቶፔ ላይ በኢንተርኔት ጎሏን አየኋት። እስከ ማግስቱ ድረስ
ምንም የማስታውሰው ነገር አልነበረም።
ከእንቅልፌ እንደነቃሁ ቁርስ በላሁ። እንደገና የጨዋታውን ሃይላይት ተመለከትኩ።
የመላው ዓለም ኮሜንታተሮችም ለይቶላቸዋል። ለካ እንዲህ የጨሰ ጎል ነበር?
በተለይ የማርቲን ቴይለር "አጉዌሮኦኦኦኦኦኦኦኦኦኦ" በጣም ወደድኩት። [ጩኸቱ
ለአራት ሰከንድ ቆየ። ይህም ለቴሌቪዥን በጣም ረጅም የሚባል ነበር።]
የድሉን ሰልፍ በግልፅ አውቶቡስ ማማ ላይ ስናደርግ 'ሻምፒዮን! ሻምፒዮን!
ሻምፒዮን!' እያልን እንዘል ነበር። ደጋፊዎቻችንን በቅርብ አየኋቸው። ጎሌ
ባመጣችው ደስታ እንዲህ መፈንጠዛቸው ያረካል። ለጥቂት ሰዓታት የሆሊዉድ
ኮከብ የሆንኩ ያህል ተሰማኝ። እስከመቼም የማይረሳኝ፣ የማይታመን ዕለት ነው።
…ለዛሬ ይሁን! ከእንግዲህ ግን በስያለሁ። በድጋሚ ዋንጫ ብናነሳ፣ ደስታዬ
በልክና በአግባብ መሆን እንዳለበት ለራሴ ቃል ገባሁ።"
………………
የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኩን አጉዌሮ ክለቡን ከ44 ዓመት በኋላ ባለክብር
ካደረገችው ጎሉ በኋላ ስለዚያች ቀን ከፃፈው መፅሐፉ የተወሰደ።
SOURCE- Mensur Abdulkeni's facebook page
No comments:
Post a Comment