የሜሱት ኦዚል ፈታኝ ጅማሬ
ፅሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው
……የጀርመን ቀኝ አክራሪ ፓርቲ NDP አፈ ቀላጤ ክላውስ ባየር "ጀርመናዊነቱ
በወረቀት ላይ ብቻ ነው" ባለኝ ጊዜ ትልቅ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ነበርኩ።
ቀድሞም ተመሳሳይ ፈተና አልፌያለሁ። ከመነሻዬ የእግር ኳስ ህይወቴ አልጋ
በአልጋ የነበረ እንዳይመስላችሁ። በማንነቴ ምክንያት ገና ከልጅነቴ አንስቶ
አድሏዊነትን አሳልፌያለሁ። ዕድሜዬ በ10 እና በ12 ዓመት መካከል ሳለ
የገንዘብ አቅም ከሚያንሳቸው ትንንሽ ክለቦች ይልቅ ለታዳጊዎች የበለጠ
የዕድገት ፕሮግራም ለነበረው ለትልቁ ሼልከ ለመመልመል በርካታ ሙከራዎችን
አድርጌያለሁ። የገጠመኝ በደል ግን አዋቂ ሆኜ ካየኋቸው መገለሎች ይልቅ የቆየ
ጠባሳ ጥሎብኝ አልፏል።
በትውልድ ከተማዬ ጊልሰንኪርሸን፣ በአካባቢዬ በሚገኝ የታዳጊዎች ቡድን
ውስጥ እጫወት ነበር። ፋልከ ይባላል። የሼልከ ገባር ወደሆነው ቶቶኒያ-ሼልከ
ለመዘዋወር የመጀመሪያ ሙከራ አደረግኩ። ትልቅ ተጫዋች ከመሆን ተነሳሽነት
ጋር ሙከራውን አራት ጊዜ ደጋገምኩት። በተርታ በተደረደሩ ቋሚ ዘንጎች መካከል
ድሪብሊንጌን አጥመልምዬ አሳየሁ። የጎል ሙከራዎቼ በግብ ጠባቂዎቹ ጆሮ
ግንድ ስር እየበረሩ ከመረቡ ተዋሃዱ። እንደኔ ምዘና ሙከራዎቼን ሁሉ በታላቅ
ስኬት አጠናቅቄያለሁ። በውጤቱ ግን ባንጋጥጥ ወፍ የለም። ከመልማዮቹ ጠብ
የሚል ነገር ጠፋ። ብቁ ነው ብሎ በእነዚያ የዕድሜ ምድቦች የሚያስገባኝ ሰው
አጣሁ።
ስሜ "ሜሱት" ከሆነው ከእኔ ይልቅ "ማቲያስ" ወይም "ማርከስ" የተባሉ
(ጀርመናዊ ስም ያላቸው) ልጆችን ብቻ የሚፈልጉ አስመሰለባቸው። እውን
በመጀመሪያ ስሜ ምክንያት ይሆን የማልመረጠው? ባዕድ በመሆኔ? ሜሱቶች
አይፈለጉም ማለት ነው? አባቴም ተመሳሳይ ስሜት አድሮበታል። ሞራላችን
እየተነካ ነው።
አንድ ቀን ከሌላ ያልተሳካ ሙከራ በኋላ ወደ ቤታችን ስንመለስ ከዚህ በላይ ምን
ማድረግ እንዳለብኝ ጠየቅኩት።
"አባዬ! እስቲ ጥፋቴን ንገረኝ። ምን አጠፋሁ? ያጎደልኩት ምንድነው?"
"ምንም አላጠፋህም የእኔ ልጅ! ከእናትህና ከእኔ በተሰጠህ ስም አንተ ምንም
ጥፋት የለብህም" አለኝ።
ለምልመላው ስኬት ደንቃራ የሆነብኝ ስሜ ብቻ አልነበረም። ከፋልከ በኋላ
ለሌላው የአካባቢዬ የታዳጊዎች ቡድን ሮት-ቬስ-ኤሰን ስጫወት የቤተሰባችን
የገንዘብ አቅም ሌላ ፈተና ሆነብኝ። ቀን መቁጠሪያው አዲሱን ሚሌኒየም
በተቀበለበት ዘመን በከተማው ሁለት ተቀናቃኝ የታዳጊ ቡድኖች መካከል የደርቢ
ግጥሚያ ነበር። ሮት-ቬስ-ኤሰን እኔን ከማግኘቱ በፊት ሁልጊዜ በሽዋርዝ-ቬይዝ
መሸነፍን ለምዷል። ለእነርሱ መጫወት እንደጀመርኩ ሰባት ጎሎች አስቆጥሬ
ሮት-ቬስ-ኤሰን 8ለ1 አሸነፈ። የመጀመሪያ የደርቢ ስኬቴ ሆነ።
እንዲህ የተሳካ ለውጥ አምጥቼ ሳለ በቀጣዩ የቡድኑ ጨዋታ ላይ ተጠባባቂ
ተደረግኩ። መሸለም ሲገባኝ ተቀጣሁ። ምክንያቱ በቡድናችን ውስጥ የነበረ
አንድ ታዳጊ ነው። የሚጫወተው እኔ በምሰለፍበት ቦታ ላይ ነው። እኔ
ከተጫወትኩ እርሱ ተጠባባቂ መሆን ግድ ይለዋል። እርሱ ከተሰለፈ ደግሞ
እንዲሁ እኔ ተጠባባቂ እሆናለሁ። በጨዋታው ወደተጠባባቂነት ያወረዱኝ
በችሎታ ማነስ አልነበረም። የልጁ አባት የገንዘብ አቅም ስላለው ቡድናችንን
በፋይናንስ ይደግፋል። በሮት-ቬስ-ኤሰን ጨዋታን ከሚያሸንፉ ጎሎች ይልቅ
ገንዘብ የበለጠ ተፈላጊ መሆኑ ታየ።
ተቃርኖው ግን ብዙ አልዘለቀም። ጥቂት ሳምንታት እንዳለፉ ከትጥቅ ድጋፍ
ይልቅ ጎሎች ይበልጥ አስፈላጊ መሆናቸውን አሰልጣኛችን ተረዳ።
ቬርነር ኪክ የክለቡ ስመጥር የቀድሞ ተጫዋች ነው። በ1960ዎቹና 70ዎቹ
ለሮት-ቬስ-ኤሰን አዋቂዎች ቡድን 293 ጊዜ ተሰልፏል። በክለቡ የክፍለ ዘመን
ታሪክ ምርጫ ውስጥ ሳይቀር ቦታ አግኝቷል። በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ኪክ ረዳቴ
ሆኖ መጣ። ያበረታታኛል፣ ይደግፈኛል፣ ይመክረኛል። እርሱን እስካገኝ ድረስ የረባ
የመጫወቻ ጫማ እንኳን አልነበረኝም። በርካሽ ዋጋ የሚገዛ ጫማ እጠቀም
ነበር። ብዙ ሳያገለግል ይቀዳደዳል። ከዚያ በኋላ ዕድሜ ለኪክ…። ደረጃውን
የጠበቀ ጫማ ተጫማሁ። ኪክ የናይኪ ጫማ ገዝቶ አበረከተልኝ። በቀዳዳ
ጫማ መጫወት ቀረ።
ዕድሜዬ 12 ነበር። እስከዚያው ይህን ያህል ብርቅ የሆነ የፉትቦል ገፀበረከት
በህይወቴ አግኝቻለሁ ብዬ መናገር የምችለው ስምንተኛ ዓመት ልደቴን ሳከብር
የተሰጠችኝ የቆዳ ኳስ ብቻ ናት። የስጦታዎቹ ትርጉም ለእኔ ቀላል
አይምሰላችሁ።
ያን ጊዜ ብርቋን ንብረቴን በየምሽቱ ቀለም እየቀባሁ ለሰዓታት እቦርሻት ነበር።
እንድትፋፋቅ አልፈልግም። በኳሷ ላይ የምታርፍ ጭረት ሁሉ ህመም ትፈጥርብኝ
ነበር። ግን የምንጫወትበት ሜዳ ጥራቱ ዝቅተኛ ስለነበር በተጫወትኩ ቁጥር
ውዷ ኳሴ መቧጨሯ አልቀረም። መጫጫሯ ሲበዛ እያንዳንዱን ውጪያዊ ሽፋን
በጥንቃቄ ልጬ በውስጠኛው ፊኛ ብቻ ተጫወትን።
በሼልከ በባዕዳን ልጆች ላይ ይደርስ የነበረው አድልኦና መገለል ለረጅም ጊዜ
ሲረብሸኝ ኖረ። ቢሆንም መጫወቴን ቀጠልኩ። በሮት-ቬስ-ኤሰን ሶስተኛ ዓመቴ
ላይ ግን ኖልበርት ኤልገርት ከተባለ አሰልጣኝ ጋር ተገናኘሁ። ኤልገርት ለትልቁ
ሼልከ ይሰራል።
15 ዓመት ሲሞላኝ ሮት-ቬስ-ኤሰን እኔን አሳልፎ ይሰጥ ዘንድ ጥያቄ ቀረበለት።
ኤሰን የተባለ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለብ ጭራሹኑ ፕሮፌሽናል ሊያደርገኝና በወር
4ሺህ ዩሮ ሊከፍለኝ ሃሳብ አቀረበ።
4ሺህ ዩሮ?… እንዴ? ይህማ የመላ ቤተሰቤን ህይወት የሚቀይር ገንዘብ ነው።
በአንድ ጀንበር ይለውጠናል። ጥያቄው ሲመጣ በሮት-ቬስ-ኤሰን ይከፈለኝ
የነበረው በወር 150 ዩሮ ብቻ ነበር። እሱም ቢሆንኮ ለእኔ ብዙ ነበር። ቤቴ
ከልምምድ ማዕከላችን 20 ኪ·ሜ ቢርቅም - ዕድሜ ለቬርነር ኪክ -
የትራንስፖርት ወጪ የለብኝም። ኪክ ችግሬን አይቶ 16 ዓመት ለሞላቸው
ታዳጊዎች ብቻ የሚፈቀደውን መመላለሻ ሰርቪስ ገና ከ13 ዓመቴ ጀምሮ
አስፈቅዶልኛል። በወቅቱ የአውቶቡሱ ሹፌር ለእኔ የተሰጠውን ልዩ ፍቃድ
ሳያጤን "እኔ… የመዋዕለ ህፃናት ልጆችን የማመላለስ ግዴታ አለብኝ እንዴ?"
እያለ ይነጫነጭብኝ ነበር።
በኤልገርት ምክር የኤሰንን ጥያቄ ውድቅ አደረግነው። ሮት-ቬስ-ኤሰንን
ከለቀቅኩ ከትምህርት ቤቴ እርቃለሁ። በትምህርት ቤቱ ደግሞ ከቀለም
ትምህርቱ በተጓዳኝ በተሰጥኦ ለታደልን ሶስት ታዳጊዎች ኤልገርት ራሱ
ተጨማሪ ስልጠና ይሰጠን ነበር።
ኤልገርት በሼልከ ተስፋ እንዳደርግ ይፈልጋል። እኔ ደግሞ ቂም አለብኝ። በለጋ
ዕድሜዬ ላየው የማይገባ አድልኦ ያደረሰብኝን ክለብ እንዴት ልመነው? ያውም
በሮት-ቬስ-ኤሰን ነገሮች በጥሩ ሁኔታ እየተጓዙልኝ ሳሉ የሼልከን በደል እንዴት
ይቅር ልበል?
እኔም ሆንኩ አባቴ ኤልገርትን አመንነው። ሁሉን መርሳት ነበረብን።
አንድ ቀን ከአባቴ ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልግ ነገረኝና በከተማው አንድ ፐብ
ቀጠሮ ያዝን።
"እውን ልጄ ተሰጥኦ አለው ብለህ ታምናለህ?" አባቴ ለኤልገርት ያቀረበው
ጥያቄ ነበር።
"ሜሱት አካላዊ ድክመቶች አሉበት። ደቃቃ ነው። በቀኝ እግሩና በቴስታ ብቃቱ
ላይ መስራት ይኖርብናል። እነዚህን ድክመቶች ካሻሻልናቸው በተቀረ ችሎታው
ድንቅ ነው። ስለዚህ በሼልከ ታዳጊ ቡድን ውስጥ ወዲያውኑ ቋሚ ቦታ ያገኛል
ብዬ ወይም ፕሮፌሽናል ስለመሆኑ ከወዲሁ ዋስትና አልሰጥዎትም።
"ስማኝ ሜሱት… አንድ ነገር ግን ቃል እገባልሃለሁ። ፉትቦልን የመረዳት፣
የአካላዊ ዝግጁነት፣ የአእምሮ ፍጥነት፣ ስሜትን የመቆጣጠርና የቡድን
መንፈስን የተመለከቱ አስፈላጊ ስልጠናዎችን እሰጥሃለሁ። ከዚያ ውጭ ሌላ
ምንም ዋስትና ላቀርብልህ አልችልም።"
…ወደ ቤታችን ስንመለስ በተስፋ ተሞላሁ። መገለል የደረሰብኝ ገና ለጋ ሳለሁ
ነው። ገና በ10፣ 11፣ 12 ዓመቴ እንደዚያ አይነት ማሸማቀቅ አይገባኝም ነበር።
ኤልገርት ግን ሩቅ አሳቢ ብልህ ሰው ነበር።
***
…ተስፋዬ እውን እስኪሆን በሮት-ቬስ-ኤሰን መጫወቴን ቀጠልኩ። በታችኛው ሪን
ክልል የታዳጊዎች ሊግ ላይ በተጫወትኩ ቁጥር ኤልገርት ይመጣል፣
ይመለከተኛል። ለሼልከ ታዳጊ ቡድን እንድፈርም ማግባባቱን ቀጠለ። በአንድ
ጨዋታ ላይ እንዲሁ በሜዳው ዳር ላይ ሆኖ ቀና ባልኩ ቁጥር ሲያየኝ አየዋለሁ።
እይታው ሁሉ በእኔ ላይ ነበር። ጨዋታው ሲያበቃ የቡድኔን አሰልጣኝ ለምክር
ፈለግኩት።
"ሼልከ ሊያስፈርምህ ቢፈልግ፣ በእኔ ቦታ ብትሆን፣ ምን ታደርጋለህ?"
አሰልጣኜ ሳይዘገይ መልስ ሰጠኝ።
"ሂድ! ሂድ! አድርገው።"
ጥቂት ሳምንታት እንዳለፉ ኤልገርት ወደ ሼልከ የታዳጊ ተጫዋቾች ማደሪያ
ሆስቴል ጋበዘን። ከዚያች ቀን በኋላ እኔና አባቴ ሰውየው ሃቀኛና መልካም ሰው
መሆኑን ይበልጥ አመንን። ውሳኔያችን እንዳልተሳሳተ ገባን። ጉዳዩ ከስሜ
ሳይሆን ከችሎታዬ ነበር። በ2005 ሮት-ቬስ-ኤሰንን ለቀቅኩ። ወደ ሆስቴሉ
ገባሁ። ከሼልከ ታዳጊዎች ዘንድ ተቀላቀልኩ። ገባሁ፣ ገብቼም በዚያው ቀረሁ።
………ወደ ጀርመን ከተሰደደ ቱርካዊ ቤተሰብ የተገኘው የሜሱት ኦዚል የፕሮፌሽናል
ተጫዋችነት አጀማመር አንዴት ውስብስብ እንደነበረ ራሱ ከተረከው መፅሐፍ
ተወስዶ ለሃገራችን አንባቢዎች እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ።
Source- Mensur Abdulkeni's facebook page
No comments:
Post a Comment