Moments:
የጅንኑ ካንቶና ሰዓት "ይለያል" (የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ማስታወሻዎች)
"...የባት ማን ፊልም ለዕይታ የወጣበት የመጀመሪያ ቀን መላ የማንቸስተር
ዩናይትድ ቡድን አባላት ሲኒማ ቤት እንድንገኝ ታዘዝን። በክለቡ የቀረበ ግብዣ
እንደመሆኑ በጥቁር ከረባት መምጣት ግድ ነበር። ሁላችንም በጥቁሩ ሽክ ብለን
በቦታው ተገኘን። ኤሪክ ካንቶና ግን በሙሉ ነጭ ሱፍና በደማቅ ቀይ ስኒከር
ከተፍ አለ። ደነገጥን። ኤሪክ ያሻውን ቢያደርግስ የትኛው ልባም ይናገረዋል?
ካንቶና ራሱ የነገሠበት፣ ራሱ የሚያዝበት የብቻው ዓለም አለው። ከሊድስ
ዩናይትድ ከተዘዋወረ በኋላ በማንቸስተር ዩናይትድ እንግዳ ነገሮች ተከታትለው
መታየት ጀመሩ።
እርሱን ለመሆን የምንመኘው አይነት ተጫዋች እንደሆነ ለማወቅ
ግን ጊዜ አልፈጀብንም። ኤሪክ ሲገባ በክፍሉ ያለ ሁሉ ቀጥ ይላል። አብረን
ከተጫወትንባቸውና ልምምድ ከሰራንባቸው ከእነዚያ ሁሉ ቀናት መካከል
(አንድም ሁለትም ቃላት እዚህም እዚያም ከመለዋወጥ በስተቀር) በአንዱም ቀን
ከኮስታራው ኤሪክ ጋር ማውራታችንን አላስታውሰውም። እኔ ብቻ ሳልሆን
ማንኛችንም አነጋግረነው አናውቅም።
የራሱ ዓለም እንዳለው አምነን ተቀበልን። ከልምምድና ከጨዋታዎች በኋላ
ሳይዘገይ እብስ ብሎ ይጠፋል። ወደ ልምምድ ሲመጣም ትንሿን ቮክስሆል
እያሽከረከረ ይደርሳል። ሲያልቅም ወደ ቮክስሆሏ ገብቶ ከዕይታችን ይሰወራል።
አናነጋግረውም። ስለእርሱ ግን ዘወትር እናወራለን። ኤሪክ ልዩ መሆኑን
እናውቃለን። አሌክስ ፈርጉሰንም ይለያል ብሎ ተቀብሎታል።
ከካንቶና ጋር ልምምድ መስራት በራሱ ትምህርት ቤት መግባት ነው። በተለይ
ለብቻው አቅልሎ ሲሰራ ማየት በአግራሞት አፍ ያስከፍታል። የራሱ አብዶዎች
አሉት። ኳሷን በቻለው ጉልበት ወደ ላይ አክርሮ ይመታትና በፍጥነት ተምዘግዝጋ
ስትወርድ መልሶ ይቆጣጠራታል። አልያም ከግድግዳ ጋር ይጫወታል። ጠበቅ
አድርጎ እያላተማት እንደገና ኮንትሮል ያደርጋታል።
አንድ ምሽት ከጨዋታ በኋላ የቡድኑ አባላት በአንድነት በጭፈራ ክለብ
እንድናሳልፍ በፎር ሲዝንስ ሆቴል ተጠራን። የመሰብሰቢያው ሰዓት ከምሽቱ
12:45 ላይ ነበር። ሁሉም በቦታው ቢገኝም ኤሪክ ካንቶና ብቻ በሰዓቱ
አልደረሰም። 1:00 ሰዓት ሲሞላ እንደረፈደበት ሰው ሳይቸኩል ጀነን እያለ መጣ።
ሪያን ጊግስ ወደ እርሱ ጠጋ ብሎ "ኤሪክ… አንድ ሰዓትኮ ነው!?" በማለት
መዘግየቱን ሊያስታውሰው ሞከረ። በልምምድ አንድ ደቂቃ ያረፈደ በሚቀጣበት
የፕሮፌሽናሉ እግር ኳስ ዓለም 15 ደቂቃ መዘግየት ይቅርታ የሌለው ሃጢአት
ነው።
"12:45 ነው" አለ ኤሪክ ኮስተር እንዳለ።
ጊግስ ሰዓቱን በድጋሚ ተመለከተ። ለውጥ የለም። አንድ ሰዓት መሙላቱን
ያሳያል።
ሪያን ሌላ ቃል ካንደበቱ ሳይወጣ ካንቶና የሸሚዙን ኮሌታ አቁሞ ሁላችንም
ከዚህ በፊት አይተነው የማናውቀውን ውብ ሮሌክስ ሰዓቱን አሳየን።
ፈገግ ብሎ የተናገረውን ደገመው።
"ኖ! 12:45 ነው" አለ።
ጊግስ ካሰረው ርካሽ ሰዓትና ከካንቶና ውድ ሰዓት ሊሳሳት የሚችለው የትኛው
ነው? ካንቶና ቃል ሳይተነፍስ መጠየቅ የፈለገው ይህን ነበር። ጊግስ መልስ
አጣ።
ሙግቱ ሳይረዝም በዚያው ተቋጨ።…"
……………
ዴቪድ ቤካም በግለ ታሪክ መፅሐፉ ላይ ወጣቶቹ የዩናይትድ ተጫዋቾች ከኤሪክ
ካንቶና ጋር ስላሳለፉት የመጀመሪያ ሲዝን ከተረከው ተወስዶ ለሃገራችን
አንባቢዎች በሚመች መልኩ የቀረበ።
ፅሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው
SOURCE - MENSUR ABDULQENI'S FACEBOOK PAGE
No comments:
Post a Comment