Saturday, June 8, 2019

የፖቼቲኖ ህይወት የተቀየረበት የሌሊት ጉብኝት

Moments:
የፖቼቲኖ ህይወት የተቀየረበት የሌሊት ጉብኝት  (የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ማስታወሻዎች)



…በመርፊ ከተማ ላይ ክረምቱ ከብዷል። ከሌሊቱ 7:00 ላይ የመኖሪያ ቤታችን በር ተንኳኳ። እናቴ ከመኝታዋ ባንና ተነሳች። በዚያ ውድቅት ሌሊት የሚመጣ ጥቁር እንግዳ ማን ይሆን? ወደ መግቢያው በር ሄዳ "ማነው?" ስትል ጠየቀች።
"እኛ፣ እነ እገሌ ነን።… እመቤት ይክፈቱልን።"
እናቴ የሚያንኳኩትን ሰዎች ማንነት ብታውቅም ፈጥና መክፈት አልፈለገችም። አባቴን ቀሰቀሰችው። አባቴም ስለሰዎቹ ቀድሞ ሰምቶ ስለነበር ከፈተላቸው።
ወደ ውስጥ ዘልቀው ቡና እንዲጠጡ ጋበዛቸው።
* * *
"……ትውልዴም ዕድገቴም መርፊ ከተማ ስለሆነ ገና የእግር ኳስን ሀሁ ከጀመርኩበት ቀን አንስቶ ለመርፊ እግር ኳስ ክለብ ወይም ለኒዌልስ ኦልድ ቦይስ መጫወት ምኞቴ ነበር። በአርጀንቲና ሳንታፌ ክፍለ ሃገር ከምትገኘው
ከዚህች ከተማ በዕድሜ ሶስት፣ አራት ዓመት የሚበልጡኝ ሁለት ልጆች ለትልቁ ሮዛሪዮ-ሴንትራል መጫወት ችለዋል። በተለይ ዴቪድ ቢስኮንቲ የተባለው ተጫዋች ለከፍተኛው ሊግና ለብሔራዊ ቡድኑም ጭምር ደርሷል።እነዚህ ልጆች እኔም ለሮዛሪዮ እንድጫወት ይገፋፉኝ ነበር። አንድ ቀን ግብዣውን ተቀብዬ አብሬያቸው ልምምድ ሰራሁ። ወዲያውም ክለቡ ሊያስፈርመኝ እንደሚፈልግ ተነገረኝ። በዚያ ሰዓት ዕድሜዬ ገና 13 ዓመት ስለነበር ትምህርቴን
በታህሳስና ጥር ወር ገደማ ካልጨረስኩ በስተቀር ልፈርም አልችልም። ስለዚህ ገባ ወጣ እያልኩ ከእነርሱ ጋር ልምምድ መስራቴን እንድቀጥል አግባቡኝና ተስማማን።
ከሮዛሪዮ ከተማ በ160 ኪ·ሜ ርቃ በምትገኘው መርፊ ልኑር እንጂ ከቤቴ 20 ኪ·ሜ ርቆ በሚገኝ ትምህርት ቤት የግብርና ሳይንስ እያጠናሁ ነበር። ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ለሮዛሪዮ ገባ ወጣ እያልኩ ልምምድ መስራቴን ቀጠልኩ።
ከቤቴ ማልጄ በ12:00 ሰዓት እወጣለሁ፣ አመሻሽ 11:00 ሰዓት ላይ እመለሳለሁ። መንገዱ ሶስት ሰዓት ይፈጃል። ብዙውን ጊዜ በጉዞዬ ላይ እንቅልፍ ይወስደኛል፣ አልያም ከሰዎች ጋር እያወራሁ እጓዛለሁ። አውቶቡሱ እንደ ወተት
አዳይ በየፌርማታው ስለሚቆም ያ ጉዞ እጅግ አታካች ነበር።
አለፍ አለፍ እያልኩ ወደ ሮዛሪዮ ልምምድ ማዕከል ስሄድ ከስልጠና በኋላ በመኖሪያ ካምፓቸው አድራለሁ። በማግስቱ ጠዋት እነሳና እንደገና ልምምድ ሰርቼ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ። በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ
በትውልድ ከተማዬ እጫወታለሁ። ሰኞ ሲመጣ ደግሞ በድጋሚ ያው ሂደት ይደገማል።
ከእነዚያ ሰኞዎች በአንዱ የሮዛሪዮ-ሴንትራል የደርቢ ተፎካካሪ የኒዌልስ ኦልድ ቦይስ አሰልጣኞች ማርሴሎ ቢዬልሳና ሆርጌ ግሪፋ ከመርፊ ከተማ 50 ኪ·ሜ
ርቀት ላይ በምትገኘው የቪያ ካናስ ከተማ የወጣቶች ምልመላ ሙከራ አዘጋጁ። በከተማዋ ጥሩ ተጫዋች መሆኔን የሚያውቅ አንድ አሰልጣኝ ስለነበር አባቴ
ይዞኝ ሄዶ እንዲያስሞክረኝ ጠየቀው። ያን ሰሞን ይሄው አሰልጣኝ ከእነቢዬልሳ ጋር ምሳ ሲበላ በማዕዱ ዙሪያም
ለምልመላ ሊጠቆም የሚችል ተጫዋች አይቶ እንደሆነ ጠየቁት። "አዎ! አንድ ልጅ አለ። ግን ምን ያደርጋል? በሮዛሪዮ ሴንትራል እየሰራ ስለሆነ ወደ ሙከራው
አልመጣም" አላቸው።
"ሮዛሪዮ?…" ሁለቱ ሰዎች ፊት ለፊት ተያዩና "መሆን የለበትም!" አሉ።
ቢዬልሳና ግሪፋ ባለተሰጥኦ ወጣቶችን ለመመልመል የቀራቸው ጥግ የለም።
መላው ሃገሪቷን አስሰዋል። እናም ይህን ጥቆማ በቀልድ አላዩትም።
"የት ነው የሚኖረው?" አሰልጣኞቹ ጠየቁ። የምኖርበት ከተማ ተነገራቸው።
* * *
አሰልጣኞቹ ከእኩለ ሌሊት በኋላ በመርፊ የነዳጅ ማደያ አካባቢ ደርሰው ጥቂት
ተላላፊዎችን ቤታችንን ያውቁ እንደሁ ጠየቁ። ቤቱን አግኝተው፣ በር ቆርቁረው
አባቴ አስገባቸው።
ለአምስት፣ አስር ደቂቃዎች ያህል ከተጨዋወቱ በኋላ የሚያወሩት ሲያልቅባቸው
"ልጁ የታለ? ማየት እንችላለን?" በማለት ወደመጡበት ጉዳይ ገቡ።
ሌሊት ቢሆንም ኩሩዎቹ ወላጆቼ "እንዴታ!" ሲሉ አሰልጣኞቹን ወደ መኝታ ክፍሌ
አስገቧቸው።
ድብን ብዬ ተኝቻለሁ። ነፍሴን አላውቅም። ግሪፋ ጠየቀ።
"እባክዎ እግሮቹን ማየት እንችላለን?"
እናቴ ብርድ ልብስና አንሶላውን ገለጠችላቸው። ሁለቱም ተገርመው ተነጋገሩ።
"አየኸው? እግሮቹን አየሃቸው? ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች ይመስላል።"
ቀድሞስ በውድቅት መጥተው ምን ሊሉ ኖሯል? ጠባቧ መኝታ ቤቴ እግሬን
በሚያደንቁ ሰዎች ተሞልታ ሳለ እኔ ጧ! ብዬ ተኝቻለሁ። በማግስቱ አባቴ
የሆነውን እስኪነግረኝ ድረስ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም።
አድናቆታቸው የፌዝ አልነበረም። ከዚያች ምሽት ጀምሮ ወደ ኒዌልስ እንድመጣ
አባቴ እንዲያሳምነኝ ይጨቀጭቁት ያዙ። ሮዛሪዮን ወድጄዋለሁና የኒዌልስን
ጥያቄ መቀበል አቃተኝ። መሄድ ባልፈልግም ቅሉ ለኒዌልስ የተጫወተ ጓደኛ
ያለው አያቴ አግባባኝ፣ አሳመነኝ። ሃሳቤን ቀየርኩ።
ቢዬልሳና ግሪፋን ለማግኘት ወደ ሮዛሪዮ ጉዞ ጀመርኩ። ሌላ የሶስት ሰዓት
አሰልቺ ጉዞ። የክለቡ ወኪሎች በመናኸሪያው ጠብቀውኝ ከተቀበሉኝ በኋላ
ከቢዬልሳ ጋር አስተዋወቁኝ።
"ሂድ፣ ቀይርና ወደ ሜዳ ግባ።…የትኛው ቦታ ነው የምትጫወተው? አጥቂ ነህ
አይደል?" ቢዬልሳ ጊዜ ሳይወስድ ጠየቀኝ።
"ለከተማዬ ክለብ በአጥቂነት እጫወታለሁ። ግን ቦታውን አልወደውም።
ተከላካይ ብሆን እመርጣለሁ።"
"እሺ! በተከላካይነት ትጫወታለህ። በል ግባ!"
ጨዋታው ተጀመረ። ከአምስት ደቂቃ በኋላ…፣ አራት አምስት ኳስ ብቻ እንደነካሁ
ቢዬልሳ ጠራኝ።
"ና!… ና! ውጣ! በቃ! ሌላ ተጫዋች ባንተ ቦታ ይገባል" አለኝ።
ኧረ! እየሆነ ያለው ምንድነው?" ብዬ ደነገጥኩ። ገና በአምስት ደቂቃ?!
ቢሆንም የታዘዝኩትን አደረግኩ።
"ጎረምሳው ወዲህ ና! እዚህጋ አረፍ በል።"
ቢዬልሳ ኳስ ላይ ተቀምጧል። ወደ አጠገቡ እንድቀርብ ጋበዘኝ።
"ሰማህ?!"
አሰልጣኙ ማውራቱን ቀጠለ። "በጥር ወር በማር ዴል ፕላታ የምንሳተፍበት አንድ የዙር ውድድር አለ። አንተም በ1972 ከተወለዱት ወጣቶች ቡድን ውስጥ እንድትጫወት እፈልጋለሁ" አለኝ።
"እኔንጃ…! ወላጆቼን ማማከር አለብኝ።" "አዎ! አማክርና አሳውቀን። በቃ!… አሁን ሂድና ገላህን ታጠብ። ስትጨርስ አንድ ሰው ወደ ክለቡ ስታዲየም ይወስድሃል" ሲል ድምዳሜ ላይ ደረሰ።በስታዲየሙ ውስጥ በሚገኝ ፅህፈት ቤት ስደርስ ግሪፋ ቲኬት ይዞ ጠበቀኝ። "ወደ ቤትህ ተመለስና ተማክረህ ሃሳብህን በቶሎ አሳውቀን። የመመለሻ ቲኬቱ ይኸውልህ!" ብሎ ቲኬቱን ሰጠኝ።ወደ ሮዛሪዮ የመጣሁት ጠዋት ነው። ከአምስት ደቂቃ ጨዋታ በኋላ፣ ከሰዓት በኋላ ወደ መጣሁበት ተመለስኩ። ከወላጆቼ ጋር መከርኩና ለኒዌልስ ልፈርም ወሰንኩ። ቢዬልሳ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ምን እንዳየብኝ አልጠየቅኩትም።እንደ ግሪፋ ሁሉ ከጊዜው የቀደመው ቢዬልሳ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ሁሉን አይቶ ጨረሰ። እኔም ለኒዌልስ ወጣት ቡድን ተመዘገብኩ።…
………
የቶተንሃሙ አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ለመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ክለቡ የተመለመለበትን ሂደት እንደተረከው።

ፅሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው
SOURCE - MENSUR ABDULQENI'S FACEBOOK PAGE

No comments:

Post a Comment

"ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል

 "ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል የፈረንሳዊው ኮከብ ፖል ፖግባ ወኪል የሆነው ሚኖ ራዮላ ፤ አማካዩ በክረምት የዝውውር መስኮት ወደ ቱሪን ሊመለ...