Moments:
የሜሲ የማለዳ ጭንቀት (የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ማስታወሻዎች)
ሆርጌ ሜሲ ወደ ሊዮ መኝታ ክፍል ፈጥኖ ገብቶ ልጁ ከተኛበት ወዝውዞ
ቀሰቀሰው።
"ደስ የሚል ዜና አለኝ ሊዮ! አስደሳች ዜና!" አለ ሆርጌ፣ ደስታ እያስቸኮለው።
አይኖቹ በእንቅልፍ እንደቦዙ ሊዮኔል ጠየቀ።
"ምን ተገኘ አባ! ምንድነው?"
"ቡድናችሁ በወዳጅነት ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ተጋበዘ። ወደ ሊማ (ፔሩ)
እንሄዳለን። በውድድሩ ላይ መሳተፍኮ ትልቅ ክብር ነው። ከአርጀንቲና፣ ቺሊ፣
ኢኳዶር፣ ኮሎምቢያ ሳይቀር ከሚመጡ ተጋባዥ ቡድኖች ጋር ትጫወታላችሁ ።"
ትንሹ ሊዮኔል ሜሲ ለኒዌልስ ኦልድ ቦይስ ህፃናት ቡድን መጫወት ከጀመረ
አንድ ዓመት ሞልቶታል። በዚህ ጊዜም "ሌፐርስ" አልተቻሉም።
ተጋጣሚዎቻቸውን ሁሉ እየደረማመሱ አይበገሬ ሆነዋል። የቡድኑ ታዳጊዎች ሁሉ
የተወለዱት በ1987 በመሆኑ "የ87 ማሽኖች" በሚል ቅፅል ይታወቃሉ። ማሽኖቹ
ወደ ሊማ ይሄዳሉ።
"ግን መቅደም ያለበት ይቀድማል" አለ ሆርጌ፣ የያዘውን ቢዝነስ ካርድ
እያውለበለበ።
ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ማልቪናስ በሄዱበት ጊዜ አንድ ሰው ካርዱን ሰጥቶት
ነበር።
"በቅድሚያ ምን?" ከአልጋው ሳይወርድ ሊዮ ጠየቀ።
"በቅድሚያማ ዶክተሩ ዘንድ መሄድ አለብን።"
***
በማግስቱ እናት ሴሊያ እና ሆርጌ ልጃቸውን ይዘው ወደ አንድ የህክምና ማዕከል
ሄዱ። ሜሲ በወላጆቹ ታጅቦ ወደ ማዕከሉ ገባ። የህሙማን መቀበያ ክፍሉ
ከጥቂት መቀመጫዎች በስተቀር ባዶ ነበር። በመሐል አሮጌ መፅሔቶች
የተዘረጉበት ጠረጴዛ ይታያል። ሴሊያ ሊዮን ይዛ ተቀመጠች። ሆርጌ ደግሞ
ከአጠገቡ በር ወደ ሚታይበት ጠባብ መስኮት ሄዶ ከጎኑ ያለውን ደውል ተጫነ።
ወዲያውኑ መስኮቱ ተከፈተ። ትሁት ገፅታ ያላቸው ዕድሜ የተጫናቸው ሴት ብቅ
አሉ።
"ስም?" ታካሚውን ጠየቁ።
"ሊዮ ሜሲ!"
መልሱን ሲሰሙ አሮጊቲቱ ቸኮል ብለው ወደ ውስጥ ገቡ። ሆርጌ በሴትዮዋ
ሁኔታ ግራ ተጋብቶ ወደ ባለቤቱና ልጁ ዞረ። ሊዮ በኪሱ ይዞ የመጣውን ሎሚ
አውጥቶ በወለሉ ላይ ወርወር በማድረግ ድሪብል ማድረግ ሲጀምር በሩ
ተከፈተ። ዶክተር ሽዋርዝቴይን ነበሩ። ፈገግታ በሚያሳየው ፊታቸው ሆርጌን
ተቀበሉት። በኒዌልስ ኦልድ ቦይስ ሜዳ ሳሉ ቢዝነስ ካርድ የሰጡት ሐኪም
ናቸው።
"ሚስተር ሜሲ በድጋሚ ስላየሁህ ደስ ብሎኛል" ብለው ለሆርጌ ሞቅ ያለ
ሰላምታ ሰጡት። ሊዮ ሎሚዋን ወደ ኪሱ መልሶ ዶክተሩን ተመለከተ። እናቱም
እንዲሁ መጥታ አጠገቡ ቆመች።
"ኑ ግቡ…" ዶክተሩ ሊዮና ሴልያንም ጭምር ወደ ቢሮው እንዲዘልቁ ጋበዟቸው።
"ስትጫወት አይቼሃለሁ። አንተ ባለልዩ ተሰጥኦ ተጫዋች መሆንህን ተረድቻለሁ።
እኔስ ምን እንደምሰራ ታውቃለህ?" ዶክተሩ ለትንሹ ልጅ ጥያቄ አቀረቡለት።
"አዎን አውቃለሁ። የልጆችን ቁመት ታሳድጋለህ አይደል?"
"ትክክል ነህ" አሉ ዶክተሩ እንደመሳቅ ብለው።
"በሰውነትህ ውስጥ የቁመትህን ዕድገት የሚቆጣጠረው ሆርሞን በትክክል
እየሰራ አይደለም። ግን መጨነቅ የለብህም። በርካታ ህፃናት ላይም
የሚያጋጥም ነገር ነው። በህክምና ሆርሞኑ ትክክለኛ ስራውን እንዲሰራ ማድረግ
ይቻላል።"
"ከዚያስ ቁመቴ ያድጋል?"
"አዎን! ትረዝማለህ።"
ሊዮ ዶክተሩን በአድናቆት እየተመለከት ተደሰተ።
የዶክተር ሽዋርዝስቴይን ላብራቶሪ ቀለል፣ ቅልብጭ ያለ ነው። ሊዮ በምርመራው
አልጋ ላይ ተኛ።
"ከሰውነትህ ደም ወስጄ ምርመራ ማድረግ አለብኝ" አሉት በሚያባብል
አነጋገር። ሊዮ ፈርጠም ብሎ አንገቱን በአዎንታ ነቅንቆ ተስማማ። በጥንቃቄ
መርፌውን ወደ ቆዳው ስር ላኩት። ከዚያም የደሙን ናሙና ወደ ብልቃጡ
ጨመሩት። የአባት አንጀት ሆኖ ሆርጌ ላለማየት ፊቱን አዞረ።
ዶክተሩ ከሊዮ ጋር ማውራቱን ቀጠሉ።
"ስትጫወት ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳየሁህ ጎበዝ መሆንህን ተረዳሁ።
ተጋጣሚዎቻችሁ ይንሸራተቱብሃል፣ ይጥሉሃል። አንተ ግን ምንም
አይመስልህም። ጨዋታህን ትቀጥላለህ። ከኋላ ሲገጩህ እንኳን
አትወድቅላቸውም፣ አትነጫነጭም። ይህን ሳይ ልዩ መሆንህን ተገነዘብኩ።
"ደግሞ አንድ ነገር አስተውዬብሃለሁ። ጥፋት ተሰራብኝ ብለህ በሃሰት
አትወድቅም" አሉት።
"ሊዮ መቼም ጥፋት ተሰርቶብኛል ብሎ አስመስሎ አያውቅም" በማለት ሆርጌ
ጣልቃ ገብቶ ማብራሪያ ሊሰጥ ሞከረ።
"ጌታው ፊትህን መልስ እንጂ። ጨርሻለሁኮ" አሉ ዶክተሩ።
"በተቻለ ፍጥነት ውጤቱን አሳውቃችኋለሁ" ብለው ቀጠሮ ሰጥተው ሸኟቸው።
***
"ማሽኖቹ" ወደ ሊማ ሄዱ። 13ኛው የወዳጅነት ዋንጫ በፔሩ ተጀመረ። ከሮዛሪዮ
1800 ማይልስ ስለሚርቅ በአውቶቡስ የ68 ሰዓታት፣ በአውሮፕላን ደግሞ
የሶስት ሰዓት ጉዞ ይፈልጋል።
በውድድሩ የአርጀንቲናው ተወካይ ለያዘው ምትሀተኛ ዝግጁ የሆነ ተጋጣሚ
አልነበረም። ድሪብሊንጉ አፍ ያስይዛል። ሲያንቀረቅብ ሰርከስ ይመስላል።
በመጀመሪያው ግማሽ አምስት ጎሎችን አስቆጠረ። በጨዋታው ዕረፍት ሰዓት
ወደ መልበሻ ቤት ሲገባ የሁሉም አይን ደቃቃው ታዳጊ ላይ ሆነ። ከዕረፍት መልስ
ሶስት ጎሎችን ጨመረ። "የ87 ማሽኖች" ካንቶሎአን 10 ለ 0 ድል አደረገ።
በኋላም የውድድሩ ሻምፒዮን ተባለ።
በውድድሩ ታሪክ በአንድ ጨዋታ ስምንት ጎል ያስቆጠረ ታዳጊ ታይቶ
አይታወቅም ነበር። የጥቁርና ቀዮቹ 10 ቁጥር የሚቻል አልሆነም።
***
ሊዮና ወላጆቹ የምርመራ ውጤቱን ለማወቅ በቀጠሯቸው ተገኙ። ይህን ጊዜ
ሊዮኔል በደንበኞች ማስተናገጃ የደረሰው ከሎሚ ጋር አልነበረም። ኳስ ይዞ
መጥቷል።
"ጥሩ ወሬ አዘጋጅተውልኛል?" ሊዮ ዶክተሩን ጠየቃቸው።
"እንደጠረጠርነው ምርመራው ቁመትህ እንዳያድግ የሚያደርግ የሆርሞን ችግር
መኖሩን አረጋግጧል። እኛ GHD ብለን እንጠራዋለን። ከበድ ያለ ይመስላል።
ግን በህክምና እንደሚስተካከል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ህክምናውም ከፍ
ያለ የውጤታማነት ታሪክ ያለው ነው።"
ሆርጌ፣ ሴሊያና ሊዮ በዶክተሩ ማብራሪያ ተደሰቱ። "እረዝማለሁ፣ እረዝማለሁ"
አለ ሜሲ፣ ደስታ ፈንቅሎት።
ዶክተሩ ፈገግ ብለው እጃቸውን በትንሹ ትከሻው ላይ አሳርፈው "አዎን
ታድጋለህ። ለዚህ ቃል እገባልሃለሁ" አሉት።
ሴሊያ "በጣም እናመሰግናለን ዶክተር። ህክምናውስ እንዴት ነው?" ብላ
ጠየቀች።
"ለዓመታት በየዕለቱ በመርፌ የሚወሰድ ነው" አሉና ወደ ሊዮ ዞረው "ራስህን
በየቀኑ መርፌ መውጋት ይኖርብሃል" አሉት።
ሊዮ ሳያመነታ "እችላለሁ" ሲል መለሰላቸው። የቁመቱ አለመርዘም የሜሲና
የወላጆቹ የዘወትር ጭንቀት ነበር። የእግር ኳስ ተሰጥኦው ባያጠራጥርም
ለወደፊቱ ከፍ ባለ ደረጃ እንዲጫወት ከዚህ በላይ መርዘም፣ መጠንከርና
መፈርጠም ይኖርበታል። የልጁም ሆነ የወላጆቹ የዘወትር ጭንቀት መፍትሄ
እንዳለው መታወቁ ቤተሰቡን አስደሰተ።
"ግን…" አሉ ዶክተር ሽዋርትዝቴይን። "ግን… ሁለታችሁን ለብቻችሁ ላነጋግራችሁ
እፈልጋለሁ።"
ሆርጌ ወደ ሊዮ ዞሮ ትንሹን ልጅ በወላጅ ትህትና አዘዘው።
"ለምን ከኳስህ ጋር ውጭ እየተጫወትክ አትጠብቀንም?"
ሊዮኔል ኳሱን ይዞ ወጣ።
"ስለህክምናው ዋጋ እንነጋገር ብዬ ነው። ወጪው በጣም ውድ ነው" ዶክተሩ
ቀጠሉ።
"ምን ያህል ውድ ነው?" ወላጆቹ ጉጉት በሚታይበት ሁኔታ ጥያቄያቸውን
አስከተሉ።
"በየወሩ ከ1ሺህ እስከ 1500 ዶላር ያስፈልጋችኋል።"
ሴሊያ በድንጋጤ ወደ ሆርጌ ዞራ በተስፋ መቁረጥ አይን አይኑን ተመለከተችው።
ምን አይነት ዱብዳ ነው? ከብረታ ብረት ፋብሪካ ስራው እንኳን ይህን ያህል
ገንዘብ አያገኝም። መርዶው ምን ያህል እናቲቱን እንደሚጎዳ ሆርጌ ያውቃል።
ወደ ራሱ አስጠግቷት ጥብቅ አድርጎ አቀፋት። የቻለውን ሁሉ ለማድረግ ቆረጠ።
አፅናናት።
"አይዞሽ ሊዮን አንተወውም! መላ እንፈልግለታለን! ልጃችንን አንተወዉም!
አንተወዉም!…"
.........
"ቁንጫው፣ አስደናቂው የሜሲ ህይወት" ከሚለው መፅሐፍ የተወሰደ።
ፅሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው
SOURCE - MENSUR ABDULQENI'S FACEBOOK PAGE
No comments:
Post a Comment