አቅራቢ - አብዱልቃድር በሽር (የሪሐና ልጅ)
የቀድሞ የሊቨርፑል ፥የቼልሲ ፥ የኤሲ ሚላን ፥የአትሌቶኮ ማድሪድ እና የስፔን ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የነበረው ፈርናንዶ ቶሬዝ በዛሬው ዕለት ከእግር ኳስ አለም በተጨዋችነት መለየቱን ይፋ አድርጓል።
የ35 አመቱ አጥቂ በአሁኑ ሰዓት በጃፓኑ ክለብ ሳጋን ሱ በመጫወት ላይ የነበረ ሲሆን በማህበራዊ ድህረ ገፆቹ ነው ከእግር ኳስ መሰናበቱን ይፋ ያደረገው።
"አሁን ይፋ የማደርገው ለየት ያለ ነገር አለ።ከ18 አስደሳች አመታት በኋላ ፥ ከእግር ኳስ ጋር የምለያይበት ትክክለኛው ጊዜ ነው።በቀጣዩ እሁድ በቶክዮ ስለ ዝርዝሩ ጋዜጣዊ መግለጫ የምሰጥ ይሆናል ፥ እዛው እንገናኝ" በማለት ነው የፃፈው።
ቶሬዝ የጃፓኑን ክለብ የተቀላቀለው 2018 ላይ የልጅነት ክለቡን አትሌቲኮ ማድሪድ ከለቀቀ በኋላ ነው።32 ግቦችንም ለኤዥያው ክለብ አስቆጥሮ ነበር።
ድንቁ አጥቂ ኤል ኒኖ የእግር ኳስ ህይወቱን የመጀመሪያ ጨዋታ አሀዱ ያለው 2001 ላይ በሁለተኛው ዲቪዥን የአትሌቲኮ ማድሪድን ማሊያ በመልበስ ከሌጋኔስ ጋር ነበር።
በሳምንቱም ከአልባሴቴ ጋር በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያ ግቡን ለክለቡ ያስቆጠረ ሲሆን ፍራሽ አዳሾቹ ወደ ስፔን ላሊጋ እንዲያድጉም አድርጓል።
ከዚያም በስፔን ካሉ ታላላቅ አጥቂዎች ውስጥ አንዱ በመሆን ለአምስት ተከታታይ አመታት የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆነ ፥ ይህም ወደ ሊቨርፑል እንዲመጣ ምክንያት ሆነው።
አንፊልድ ከደረሰ ወዲያም የተጨዋችነት ህይወቱን አስደናቂ ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን ባልተጠበቀ ሁኔታ 2011 ላይ የዝውውር መስኮቱ ሊጠናቀቅ ሰዓታት ሲቀሩት ወደ ቼልሲ እስኪዘዋወር ድረስም ለቀያዮቹ በ142 ጨዋታዎች 81 ግቦችን ከመረብ አዋህዷል።
ቼልሲ ከገባ በኋላ ግን አጀማመሩ አላማረም ነበር።በ2010/11 የውድድር ዘመንም በመጀመሪያዎቹ 18 ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ነበር ያስቆጠረው።
በሰማያዊዎቹ ቤት በነበረው ቆይታ 2012 ላይ ኤፍ.ኤ ካፕ እና ሻምፒዮንስ ሊግን 2013 ላይም ዩሮፓ ሊግን አሳክቷል።
ከዚያም ስድስት ወራትን በጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ካሳለፈ በኋላ ወደ ልጅነት ክለቡ አትሌቲኮ ማድሪድ ተመልሷል።2018 ላይም ወደ ጃፓን ከመሄዱ በፊት ከአትሌቲኮ ጋር ዩሮፓ ሊግን አሳክቷል።
በኢንተርናሽናል መድረክም ለሀገሩ ስፔን እጅግ ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል።ሀገሩ 2008 እና 2012 በተከታታይ የአውሮፓ ዋንጫን እንዲሁም 2010 ላይ የዓለም ዋንጫ ስታሳካ ከስኳዱ ወሳኝ ተጨዋቾች አንዱ ነበር።
ኤል ኒ ኖ በአንድ ወቅት የተከላካዮች ራስ ምታትም ነበር ፥ ያየነው እናውቀዋለን ……
No comments:
Post a Comment