የሱአሬዝ የስኬት ምስጢር - ውሃ!
ፅሁፉ - የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው
... በሊቨርፑል ከየጨዋታው ማብቂያ በኋላ ፊዚዮዎቹ ለየተጫዋቹ ስሙዚ ያድላሉ። ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ወደእኔ እየመጡ "ሱዋሬዝ ምን አይነቱ ቃና ይሻልሃል?" ብለው መጠየቃቸው የዘወትር ልማድ ነበር።
"በቼኮላት ወይስ በፍራፍሬ ቃና? በየትኛው ይዘጋጅልህ?"
ስሙዚው ቢመጣልኝ እንኳን አልጠጣውም። ቢቀዳም መደፋቱ የማይቀር ነው።የሁልጊዜም ምርጫዬ ውሃ መጠጣት ነው። ብዙ ውሃ፣ በጣም ብዙ ውሃ እጠጣለሁ። በሆላንድ፣ ለአያክስ በምጫወትበት ጊዜ መጠጣት ጀመርኩ፣ ከዚያ በኋላ እስካሁን አላቆምኩም።
በጨዋታ ቀን አሁንም ውሃ አብዝቶ መጠጣት ምርጫዬ ነው። ፉት እላለሁ፣።ከእጄ ላይ ውሃ አይጠፋም። ከጨዋታ በፊት የምጠጣውን የውሃ መጠን ፊዚዮዎቹ ሲሰሙ ማመን ያቅታቸዋል። በቀላሉ አራት፣ አምስት ሊትር ውሃ
እጨርሳለሁ። ውሃ ብቻ አይደለም። ዬርባ ሜት (የላቲን አሜሪካዊያን ባህላዊ ሻይ) ስለማዘወተር የሰውነቴ የፈሳሽ መጠን በጨዋታ ሰዓት ላይ ዘወትር ከፍ ያለ ነው።
በጨዋታ ጊዜ ሁሉን ነገር ስለምትረሳው አይታወቅህም። ጨዋታው ካበቃ በኋላ ግን ወደ መፀዳጃ ቤት መመላለስ ልማዴ ነው። አሁንም አሁንም ለሽንቴ መግባት መውጣቴ ግድ ነው። ከጨዋታ በኋላ ባለቤቴን ያገኘኋት እንደሆነ "ቆይ
መጣሁ፣ አንድ ጊዜ..." እያልኩ ለውሃ ሽንት ከአጠገቧ ለአፍታ መለየት አመሌ ነው።
20 ደቂቃ ያህል አለፍ እንዳለም እንደገና "ቆዪ! ቆዪ! ደቂቃ አልቆይም! እመለሳለሁ! እያልኩ እብስ እላለሁ። ባለቤቴ ሶፊ በዚህ ሁልጊዜ ትበሳጫለች።
ነገሩ የቡድን ጓደኞቼ መሳቂያም አድርጎኛል። ለበረራ ኤርፖርት ሳለሁ ወይም አውቶቡስ ውስጥ መንቆራጠጤ አይቀርም። ከአጠገቧ ስነሳ "አሁንም በድጋሚ?" እያለች ሶፊ ትበሳጭብኛለች።
ለድህረ ጨዋታ ሽንት ምርመራ ስንጠራ ግን አልቸገርም። ሌሎች ተጨዋቾች የሰውነት ፈሳሽ ከሚጨርስ ጨዋታ በኋላ ለጠብታ ሽንት ናሙና ያምጣሉ። እኔጋ ችግር የለም። ገባ ብዬ፣ ወጣ ማለት ብቻ ነው።ውሃ ላብዛ እንጂ ከጨዋታ በፊት መብል ላይ እምብዛም ነኝ። የሊቨርፑል ፊዚዮዎችና የኡሯጓይ ባለሙያዎች ይገረሙብኛል። "ውሃ እንዲህ እያበዛህ፣ ምግብ በቅጡ ሳትመገብ በየጨዋታው እንዴት ይህን ያህል ትለፋለህ?" እያሉ በመደነቅ ይጠይቁኛል።
ጨዋታችን ከቀትር በኋላ 9:00 ሰዓት የሚጀምር ከሆነ ጠዋት አረፋፍጄ - 3:30 ወይም 4:00 ገደማ - ከአልጋ እነሳለሁ። ከዚያ ሜቴን መጎንጨት እጀምራለሁ።
ሜት በራሱ አንድ ሊትር ተኩል ገደማ ውሃ አለው። በዚህ ላይ ጨዋታው እስኪቃረብ ድረስ ንፁህ ውሃ መጠጣቱን ደግሞ እቀጥላለሁ። አምስት፣ ስድስት ትንንሽ የውሃ ኮዳዎችን ባዶ አስቀራለሁ። በድምሩ ሁለት ሊትር ተኩል ወይም
ሶስት ሊትር ውሃ ይይዛሉ። በዚያ ላይ አንድ ሰፊ ሳህን ፓስታ ከጨመርኩበት ይበቃኛል።
ጨዋታችን ምሳ ሰዓት ላይ ከሆነ፣ በቁርስ አንድ ቁራሽ የተጠበሰ ዳቦ ከበላሁና ሜት ከጠጣሁ በቂዬ ነው። ሌላ ምግብ አልጨምርም። በምግብ ክፍሉ ተቀምጬ ተጫዋቾች በረፋዱ አራት ሰዓት በትልልቅ ሳህን ፓስታ ሲመገቡ እያየሁ እገረማለሁ። እንዴት እሺ ይላቸዋል? ከሰዓት በኋላ ሰባት፣ ስምንት ሰዓት ቢሆን እንኳን እሺ! ረፋድ ጠዋት እኮ ነው!? በበኩሌ ንክችም አላደርገውም። ምሳ
ሰዓት ቢሆን እንኳን፣ ከጨዋታ በፊት ከሆነ ምግብ አላበዛም። ፓስታ የለ! ሼክ፣ ስሙዚ የለ! ትንሽ ሰላጣ ብቻ ይበቃኛል፣ ውሃ እጠጣለሁ። በቃ!
ፊዚዮዎች፣ የስነምግብ አዋቂዎች፣ ማናጀሮችና አሰልጣኞች ሁሉ ምግብ በደንብ እንድበላ ያበረታቱኛል። ግን ከንቱ ድካም ይሆንባቸዋል። የጡንቻ ጉዳት ለምን ደጋግሞ እንደማያስቸግረኝ በማሰብ ግራ ይጋባሉ። ነገሩ ከሳይንሱ ጋር አይጣጣምም። ከጨዋታ በኋላ ለፈጣን ላብና ጉልበት መተኪያ እስከጠቀመ ድረስ በጥንቃቄ የተቀመመ ስሙዚ መጠጣትን አልቃወምም። ለራሴ ግን አይሆንልኝም፣ በጠጣሁ ቁጥር ያመኛል። ምቾት አይሰጠኝም። ለእኔ ሁሉ ነገሬ ውሃ ነው። ከጨዋታ በፊት ውሃ፣ በዕረፍት ሰዓት ውሃ፣ ጨዋታ እንዳለቀ ውሃ። ይህ እየታወቀ ጨዋታ በተጠናቀቀ ቁጥር የቡድኔ ባለሙያዎች መጠየቃቸውን አያቆሙም።
"ሱዋሬዝ የትኛውን ይሁንልህ? በቼኮላት ወይስ በፍራፍሬ ቃና?" መልሱን እያወቁትም ይጠይቁኛል።
......
ሉዊስ ሱአሬዝ ራሱ ከተረከው ግለ ታሪክ የተወሰደ።
Source - Mensur Abdulkeni's Facebook Page
No comments:
Post a Comment