Moments:
ሆንሪ፣ ኢኒዬሽታና የፓሪሷ ምሽት (የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ማስታወሻዎች)
ፍራንክሊን ኤድሙንዶ ራይካርድ በፓሪስ ቡዋስ-ደ-ቡሎኝ ምሽት ክበብ ሲጋራ
ለማጨስ ሲል ወደ ክፍሉ ጥግ ሄዶ ተቀመጠ። ክበቡ በሰዎች ተሞልቷል። ጭሱ
ከኩባ ሰራሹ ሲጋራ ጫፍ ላይ በቀስታ ይንቦለቦላል። አሰልጣኙ ረጋ ብሏል። የድል
አድራጊነት እርጋታ፣ የእፎይታ እርጋታ፣ ተልዕኮን በስኬት የማጠናቀቅ እርጋታ
ይስተዋልበታል። ፉትቦል ክለብ ባርሴሎና በቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ካነሳ ገና
ሁለት ሰዓታት ያህል ቢሆነው ነው…፣ ፓሪስ፣ 2006።
የክለቡ ፕሬዚዳንት ሆዋን ላፖርታ በደስታ ሰክረው፣ በዳንሱ መድረክ ላይ ማይክ
ጨብጠው ሲያንጎራጉሩ ዓለምን በንጉሥነት የሚገዙ ይመስሉ ነበር።
ራይካርድ በባርሳ አሰልጣኝነት የተሾመው በድንገት ነው። ስፖርቲንግ ዳይሬክተር
ትኪቺ ቤጉርስቴይን የዮሃን ክራይፍን ምክር ሰምቶ ቅጥሩን ቢፈፅምለትም የሃገሩን
ክለብ ስፓርታ ሮተርዳምን ይዞ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ከወረደ ብዙ አልቆየም
ነበር። ያቺ ምሽት ግን ራይካርድ በሮናልዲንሆ ፈገግታ ላይ ጋልቦም ቢሆን
የቻምፒየንስ ሊግን ክብር ከተጎናፀፈ በኋላ የመጣች፣ የእግር ኳስ አሰልጣኝነት
ህይወቱ ወርቃማዋ ሰዓት ነበረች። ብዙዎች በምሽት ክበቡ በፈንጠዚያ በህብረት
ሲያብዱ፣ የአውሮፓ ሻምፒዮኑ ፍራንክ ለብቻው ጭሱን ማቡነኑን መረጠ።
ድንገት ትክቺኪ ወደ እርሱ መጣ። ጠጋ ብሎትም ስላለፈው ሳይሆን ስለመጪው
ጊዜ ጠቃሚ ምክር ለገሰው።
"ፍራንክ አንድሬስን ማነጋገር አለብህ!"
***
የአውሮፓን የክለቦች ዘውድ ለመድፋት ከአርሰናል ጋር ከተደረገው ፍልሚያ
ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ ቤግርስቴይን አይኑን ማመን አቃተው። የባርሴሎናን
አሰላለፍ ሲመለከት አንድሬስ ኢኒዬሽታ የለም። ለሺሆች የባርሳ ደጋፊዎችም
ውሳኔው የተጠበቀ አልነበረም። በሩብ ፍፃሜው ከቤኔፊካ ጋር በመሐል ሜዳ
አማካይነት፣ በግማሽ ፍፃሜው ከሚላን ጋር በግራ አማካይነት ተጫውቶ
ኢንዬሽታ የቡድኑ አዲሱ ቁልፍ ሰው መሆኑን አስመስክሮ ነበር።
ከሆላንዳዊነት ይልቅ ጣልያናዊነት የሚታይበት ራይካርድ ግን ኢኒዬሽታን ትቶ
ኤድሚልሰን፣ ዴኮና ቫን ቦመልን አሰልፏል። ቻቪ በጉዳት የለም። ኢኒዬሽታ ወደ
ተጠባባቂነት ወርዷል። በአሰላለፉ ውስጥ ሶስት የላ ማሲያ ልጆች ብቻ ይገኛሉ።
ሶስቱም ግን የተሰለፉት ከኋላ ነበር። በረኛው ቫልዴስ፣ ተከላካዩ ፑዮል እና
የመስመር ተከላከዩ ኤሌጉዌር።
የኢኒዬሽታ አባት ሆዜ አንቶኒዮ "መርዶውን" የሰሙት በአውቶቡስ ወደ ፓሪስ
እየመጡ ነበር። እንዴት ሊሆን ይችላል? ሲሉ በልጃቸው ተጠባባቂ መሆን
ተበሳጩ።
ስታዲየም ደርሰው ወደ ሜዳው ቢያማትሩ የተባለው እውነት መሆኑን አረጋገጡ።
የልጅነት ጓደኛው፣ በፎንቴያልቢያ ጎዳናዎች አብሮት እየተጫወተ ያደገው ማሪዮ
በጨዋታው ላይ ሊገኝ ወደ ፓሪስ መጥቶ ጓደኛው ከተሰላፊነት ውጭ መሆኑ
አብግኖታል።
***
በጨዋታው ባርሳ መድፈኞቹን መቋቋም ተሳነው። በ18ኛው ደቂቃ ላይ ግብ
ጠባቂው የንስ ሌህማን በሳሙኤል ኤቶ ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ
ሲወጣ ጥፋቱን ተከትሎ የሉዶቪች ዥዊሊ ጎል ተሻረች። ከዚያም በ37ኛው
ደቂቃ ላይ ሶል ካምቤል ያስቆጠራት ጎል አርሰናልን መሪ አደረገች።
የመጀመሪያው ግማሽ በእንግሊዙ ቡድን የበላይነት ሲጠናቀቅ በባርሴሎና ወገን
ድንጋጤን ፈጠረ። የአሰልጣኙ ውሳኔ ያልጠበቀው የሆነበት ኤቶ ወደ
ተጠባባቂዎቹ ቦታ ተጠግቶ ለረዳት አሰልጣኝ ሄንክ ቴን ኬት መፍትሄውን
ጠየቃቸው።
"አንድሬስ አይገባም እንዴ?"
ቴን ኬት ሳያንገራግሩ መለሱለት።
"ልናስገባው እያሰብንበት ነው።"
ኢንዬሽታ ከገባ ነገሮች በበጎ እንደሚቀየሩላቸው ኤቶ ያውቃልና ጥያቄው ተገቢ
ነበር።
***
ከዕረፍት መልስ አንድሬስ በኤድሚልሰን ተቀይሮ ከገባ በኋላ በባርሳ ማጥቃት
ጨዋታ ላይ ነፍስ ዘራበት። እንደ ሩብ ፍፃሜውና ግማሽ ፍፃሜው ሁሉ ሜዳውን
ፈነጨበት። ላርሰንና ቤሌቲ እንዲሁ ተቀይረው ተጨመሩ። ከዕረፍት በኋላ ሁሉ
ነገር ተለወጠ።
ከሚላን ጋር ሲጫወቱ፣ ከሮናልዲንሆ ጮሌነትና ከዥዊሊ ብቃት ጋር ኢኒዬሽታ
የባርሳን የውብ ጨዋታ ቅላፄ በባርሴሎናዊ ቅኝት ያለ እንከን አቀንቅኖታል።
ለፍፃሜው ባለፉ ማግስት ዕለታዊው ሌኪፕ ጋዜጣ ኢኒዬሽታ ላይ ያነጣጠረ
የአድናቆት ቅኔ የተቀኘለት በዚያ ምክንያት ነበር።
"ከሮናልዲንሆ ጋር ኢኒዬሽታ የባርሴሎና ፍሪ-ስፒሪት ነው። እንደ እባብ በዝምታ
አድብቶ ያጠቃል። ይህን አይጨበጤ ትንሽ ሰይጣን እንዴት ማቆም ይቻላል?"
የጋዜጣውን የአድናቆት ጥያቄ አርሰናሎችም መመለስ አቃታቸው። መድፈኞቹ
አፈገፈጉ። ካታላኑ ሁለት ጎል አስቆጥረው መሪነቱን ተቆጣጠሩ። የአርሰናሉ
አምበል ቲዬሪ ሆንሪ የለንደኑን ክለብ ለአውሮፓዊ ክብር አብቅቶ ይሰናበተው
ዘንድ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ነበረበት። ግን ምኞቱ አልሰመረለትም።
እስከዛሬም በመጥፎ ትዝታ ያስታውሰዋል።
"ስለዚያ ጨዋታ ሳላስብ የመሸ አንድም ቀን የለም። ለምን? ቢባል፣ አርሰናል
ያንን ዋንጫ አሸንፎም ሆነ ለፍፃሜ ደርሶ አያውቅምና ታላቅ ዕድል ነበር።
ጨዋታው የተስተናገደው በሃገሬ ምድር፣ ከትውልድ ሰፈሬ 30 ኪሎ ሜትር እንኳን
በማይርቅ ስታዲየም ነው። መላው የቤተሰቤ አባላት በስታዲየሙ ታድመዋል።
ከሁሉም በላይ ሁሉም የሚያወራው በተከታዩ የውድድር ዘመን ወደ ባርሴሎና
ላደርገው ስለምችለው ዝውውር ነበር። እናም እንግዳ ቀን ሆኖብኝ አለፈ።
"ሁልጊዜም በአእምሮዬ የሚመላለስ ሃሳብ አለ። (ሌህማን በቀይ ካርድ
ሳይወጣ) የተጫወትነው 11-ለ-11 ቢሆንስ ኖሮ? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። እሺ፣
ዥዊሊ ጎሉን ያስቆጥረውና በረኛው (ሌህማን) ግን ቀይ ካርድ አይመልከት፣
ከዚያ 11-ለ-11 ተጫውተን ቢሆንስ ኖሮ?…"
ከወራት በኋላ ሆንሪ ለባርሳ ቲቪ ይህን ሲናገር ንግግሩን ሳያቆራርጥ መጨረስ
አልቻለም። አንድ በአንድ በፓሪሱ ፍፃሜ ላይ የሆነውን ሁሉ አይዘነጋም። ረጅም
ኳስ፣ አጭር ኳስ፣ ከሩቅ የተመቱ የጎል ሙከራዎች፣ የቅርብ ርቀት ጎል
የማስቆጠር ጥረቶች፣ የቫልዴስ አስደናቂ ማዳኖች… ሁሉ በሆንሪ ህሊና
ይመላለሳሉ።
"እውነት ነው" ይላል ቲቲ ስለዚያች የፍፃሜ ምሽት መናገሩን በመቀጠል።
"እውነት ነው። ለጎል የምንመታው ሁሉ የቪክቶር ቫልዴዝ እጅ ላይ ይቀር ነበር።
ይሁን እንጂ ዋናው ልዩነት ፈጣሪሌላ ሳይሆን አንድ ሰው ነበር። እርሱ ሲገባ ሁሉ
ነገር ተቀየረ። ኤድሚልሰንና ቫን ቦሜልን መከላከል ችለን ነበር። አንድሬስን
ግን……"
ሆንሪ ሃሳቡን አልቋጨም። ቀጠለ።
"ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ ጭራውን መያዝ አቃተን። እኛ 10 ነበርን። እኔ በዘጠኝ
ቁጥር እና በ10 ቁጥር ቦታ፣ በፊት መስመርና አማካዩን እየረዳሁ (የጎደለውን
ለመሙላት) እጫወት ነበር። በኋላ ግን አቃተኝ። አንድሬስ ኳስ ባገኘ ቁጥር
አቅጣጫውን ይቀይራል፣ ይዞራል፣ ፈጥኖ ያመልጠናል። የላርሰንና የቤሌቲን
ነገር ሁሉ ማወቄ እርግጥ ነው። የእውነት የገደለኝ ሰው ግን አንድሬስ ኢኒዬሽታ
ነበር።…"
ምንጭ - Mensur Abdulkeni's facebook page
No comments:
Post a Comment