Moments:
እልህ፣ ቁጭት፣ ቁርጠኝነትና ታዳጊው ሮናልዶ(የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ማስታወሻዎች)
....ክሪስቲያኖ የአሰላለፍ ዝርዝሩን በአንክሮ ቢመለከተውም ስሙን አላገኘውም።
ደጋግሞ ተመለከተው። አሁንም ስሙ እንደሌለ አረጋገጠ። ከዚያ ተንሰቅስቆ
አለቀሰ። በስፖርቲንግ አካዳሚ ተመልምሎ በሊዝበን ከተማ በመኖሩ ያደገባትን
ደሴት፣ ሩቋን ማዴይራን ናፍቋል። የስፖርቲንግ አካዳሚ ከ15 ዓመት በታች
ቡድን ወደ ማዴይራ፣ ፈንቻል ሄዶ እንደሚጫወት ከቀናት በፊት ቀድሞ ተነግሮ
ስለነበር እንደ ነፍሰጡር ቀኑን ሲቆጥር ሰንብቷል። ወደዚያ መሄዱንና
የናፈቃቸውን ቤተሰቦቹንና አብሮ አደግ ጓደኞቹን እንደሚያገኝ ሲያስብ ሳምንቱን
ሙሉ ትኩረቱን በልምምዱ ላይ መሰብበስ አቃተው። ጨዋታው ግለኝነት
በዛበት። ለጓደኞቹ ማቀበል አቆመ። ኳስ ይዞ አይለቅም። ያገኘውን ሁሉ ለጎል
ይሞክራል። እግር ኳስ የቡድን ስራ መሆኑን ዘነጋው። የቡድኑ አሰልጣኝ ከተጓዥ
ዝርዝሩ ውጭ ያደረገው ለዚህ ነበር። በጉዞው ባለመካተቱም ከቡድኑ ጋር ወደ
ናፈቃት የትውልድ ከተማው የመጓዙ ታላቅ ዕድል አመለጠው።
ሌሎች ወደ ማዴይራ ሄደው እርሱ በሊዝበን መቅረቱን ማመን አልቻለም።
አለቀሰ፣ አለቀሰ፣ አለቀሰ። እምባውን አፍስሶም እልሁ ከውስጡ አልወጣልህ
አለው። ከአጠገቡ ብሶቱን የሚያማክረው ሰው አጣ። በልምምድ ላይ ጥረትህን
ሁሉ ሳትቆጥብ ካልሰጠህ ከአሰላለፍ ውጭ የመሆን ቅጣት እንዳለ ገና በማለዳ
ተማረ።
በአካዳሚው ህግ ጥፋት የፈፀመ ታዳጊ የሰልጣኞቹን የመመገቢያ ክፍል
የማፅዳትና ቆሻሻውን ሰብስቦ በጋሪ የመድፋት ግዴታ ይጣልበት ነበር። አንድ
ቀን የማዴይራው ልጅ ሮናልዶም መቀጣቱ አልቀረም። ይህን ሲያደርግ
የተመለከቱት ታዳጊዎች ተሳለቁበት።
መንጓጠጡ በዚህ ብቻ አልነበረም። ሮናልዶ ከማዴይራ ደሴት በመምጣቱ
የፖርቱጊዝ አነጋገር ዘይቤው እንደ መሐል ሃገር ሰው አልነበረም። በአካዳሚው
በእግር ኳስ ችሎታው የሚያማው የለም። አንድ ግዙፍ ተጫዋች "እየተሰራ"
እንደሆነ ሁሉም ቢረዳም በክልል ልጅነት መገለል ገጥሞታል። በአነጋገር ዘዬው
ይቀልዱበታል።
ናፖሊዮን በኦገስት 15 ቀን 1769 የተወለደው በአጃክሲዮ ከተማ፣ ኮርሲካ ደሴት
ነበር። ገና የ10 ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ ለውትድርና ነፃ የትምህርት ዕድል ወደ
መሐል ሃገር አካዳሚ ከላከው በኋላ ፈረንሳይኛን በኮርሲካ ቅላፄ በመናገሩ
በመሳፍንት ልጆች ይሾፍበት ነበር።
ነገሩ ለታዳጊው ምልምል ተማሪ መነሳሻ ሆኖት ጥረቱን ሁሉ ትምህርቱ ላይ
አዋለ። ከዓመታት በኋላም ናፖሊዮን ዓለምን ቀየረ።
ሮናልዶም እንደ ናፖሊዮን በስፖርታዊ ጀብድ ዓለምን መቀየሩ አልቀረም።
በሰልጣኝ ታዳጊዎች ፌዝ አልተሰናከለም። ጊዜ እስኪያልፍ ለውዲቷ እናቱ
እየደወለ ብሶቱን ይነግራታል። እያለቀሰ ካነጋገራት በኋላ አይኑን ጠራርጎ ወደ
አካዳሚው ይመለሳል።
በጥፋቱ ምግብ ቤቱን ሊጠርግ ተገደደ። ጥራጊውንም ሰብስቦ ከሌላ ቆሻሻ ጋር
በእጅ በሚገፋ ጋሪ አውጥቶ መድፋት ነበረበት። ቆሻሻውን ከጊቢው ውጭ ባለ
ቦታ ለመገልበጥ ጋሪዋን እየገፋ ሲወጣም አራዳ ነን ከሚሉ ልጆች ሌላ ተረብ
ገጠመው።
"ሃሃሃሃሃ… ሮናልዶ ፌራሪ እየነዳህ ነው እንዴ?" ሲሉ ተሳለቁበት።
በንዴት የጦፈው ሮናልዶ በቁጭት መለሰላች ።
"ቆይ ታያለህ…
"ቆይ ታያለህ። አንድ ቀን የዓለም ምርጡ ተጫዋች እሆንና የብዙ ፌራሪዎች
ባለቤት እሆናለሁ።"
……………
ከክሪስቲያኖ ሮናልዶ ግለ ታሪክ መፅሐፍ ተወስዶ ለሃገራችን አንባቢዎች
በሚመች መልኩ የቀረበ።
ፅሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው
SOURCE - MENSUR ABDULQENI'S PAGE
ለሀገራችን አንባቢዎች በሚመች መልኩ ስትል…
ReplyDelete