Monday, January 7, 2019

የፈርዲናንድ የህይወት ትራጀዲ

ጽሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው

Moments:
የፈርዲናንድ የህይወት ትራጀዲ
"ክቡራትና ክቡራን የዚህ ሽልማት አሸናፊ… ሪዮ ፈርዲናንድ!" የሚለው
የምስራች ከመድረክ ላይ ሲሰማ አዳራሹ በጭብጨባ ቀለጠ። ሪዮ ቄንጠኛ ሱፍ
ኮቱን ቆልፎ አጠገቡ ተቀመጠችውን ሴት ጉንጭ ስሞ ወደ መድረኩ አመራ።
ሜይ 14 ቀን 2018…።
የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበል በቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልሞች ዘርፍ
"Being Mum and Dad" በሚለው በቢቢሲ ቴሌቪዥን በተላለፈው ፊልሙ
የባፍታ ሽልማት ማግኘቱ ነበር።
ባማረው የለንደን ሮያል ፌስቲቫል አዳራሽ ለሽልማቱ ምስጋናውን ሲያቀርብ ሪዮ
እምባ ይተናነቀው ነበር።
በሜይ 2015፣ ከጥቂት ወራት የካንሰር ህመም በኋላ ሬቤካ ፈርዲናንድ ከሪዮና
ከሶስት ህፃናት ልጆቿ በሞት ተለየች። ህመሙ ፈጥኖ በመላው ስውነቷ
በመዛመቱ ለ34 ዓመቷ ሬቤካ አጣዳፊ ነበር። ባለቤቱ ባላሰበው ፍጥነት ከጎኑ
የተለየችበት ሪዮ በድንገት ሰማይ ተደፋበት፣ ምድሩ ሁሉ ጨለመበት። ህፃናቱን
ያለእናት ስለማሳደግ ማሰቡ በራሱ ዳገት ሆነበት። ልጆቹን አይውጣቸው ነገር፣
ምን እንደሚያደርጋቸው ጨነቀው።
"ህይወቴ ሁሉ ጨለማ ውስጥ ገባ። ጓዳዬ ገብቼ ለብቻዬ ተንሰቅስቄ ማልቀስ
የዘወትር ልማዴ ሆነ። አልወጣልህ አለኝ። የሚሰማኝ የተለየ ስሜት ነበር። እንደ
እግር ኳስ ተጫዋችነቴ የመልበሻ ቤት መንፈስ የተጠናወተኝ ነኝና ስሜታዊ
ጉዳቴን ለማንም ማማከር አልፈለግኩም። ለራሴው ይዤው ተብከነከንኩ።
"ልጆቼ 'እናት የሌለን ለምንድነው?' ብለው ቢጠይቁኝስ? ምን መልስ ይኖረኛል?
…በሐዘንና ጭንቀት ተጎዳሁ። ከዚህ ስሜት ለመሸሽ ከመጠን በላይ አልኮል
ማዘውተር ጀመርኩ።"
ምሽት ወደ ልጆቹ መኝታ ቤት ይገባል። አልጋቸው ጎን ሆኖ ከገጠመው ሃዘን ሌላ
ነገር ማሰብ አይችልም።
"የሬቤካ ከጎናችን መለየት ያብሰለስለኛል። ከዚያ ወደታችኛው ፎቅ እወርድና
በሃዘንና ተስፋ መቁረጥ ከአልኮል መጠጥ ጋር ግብግብ እይዛለሁ። አለቅሳለሁ፣
እጠጣለሁ፣ እጠጣለሁ፣ እጠጣለሁ…።"
ሎሬንዝ (11 ዓመት) እና ታቴ (9 ዓመት) ወንዶች ናቸው። ሶስተኛዋ ቲያ 6 ዓመቷ
ነበር። እናታቸውን ቢያጡም በአያታቸው ተፅናኑ። የሪዮ እናት መኖሪያ ቤት ልጆቹ
ለሚኖሩበት ሰፈር ቅርብ ስለነበር ህፃናቱ የአያታቸውን ፍቅር በማግኘታቸው
ደስተኞች ነበሩ። ከትምህርት ቤት በፊት፣ በኋላና በሌላም ጊዜ ህጻናቱ
የአያታቸውን ዳበሳና ምክር ለመዱ። ግን ይህም ብዙ አልቆየም። በጁላይ
2017፣ ሪዮ ባለቤቱን በሞት ከተነጠቀ ሁለት ዓመት ሳይደፍን የሚወዳት እናቱን
በተመሳሳይ በሽታ አጣ።
ካንሰር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሪዮ ፈርዲናንድን ያለ እናትና ሚስት፣ ልጆቹን
ደግሞ ያለ እናትና አያት አስቀራቸው። ልጆቹም በፈተና ውስጥ አለፉ።
"በህይወቴ ሁሉ ምሳ አዘጋጅቼ፣ ምሳ ዕቃ ቋጥሬላቸው አላውቅም። ሬቤካ
በህይወት ሳለች ማልደው ተነስተው፣ ቁርስ ተመግበውና ተዘገጃጅተው ወደ
ትምህርት ቤት ሊወጡ 10 ደቂቃ ሲቀራቸው እኔ ከአልጋዬ መነሳትን የለመድኩ
ሰው ነኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ምሳ የቋጠርኩላቸው ቀን ግን በጣም ረፈደባቸው።"
ሃዘኑ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ቤት ሰርቶበት ራሱን ስለማጥፋት ማሰብ
ጀመረ። አልኮል ማዘውተሩ ደግሞ ራስህን ግደል የሚለውን ርኩስ ሃሳብ
አበረተባት። ያን ጊዜ በርካታ ሰዎች ሊረዱት መጡ። የምክር አገልግሎትም
አላጣም። በመከራ የተልፈሰፈሰው የኳስ ሜዳ ጀግና የሚያሳሱትን ልጆቹን
እየተመለከተ ተፅናና። ለእነርሱ ሲል መኖር እንዳለበት ራሱን አሳመነ። እነርሱም
እንዲጠነክሩ የእርሱ መፅናት አስፈላጊ ነበር።
የከበደ ሃዘን ተጭኖት ከወደቀበት እንደ ምንም ሲነሳ ፈርዲናንድ "እናትም፣
አባትም ሆኖ መኖር" የሚለውን መፅሐፉን አሳተመ። የተጋፈጠው ፈተና
ተመሳሳይ ርዕስ ባለው የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልም ላይ ተተረከ። ፊልሙን ያየ ሁሉ
ሪዮን አፅናናው።
"ከፊልሙ መለቀቅ በኋላ በየመንገዱ ላይ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አዛውንቶችና
አያቶች ሲያገኙኝ ስለእግር ኳስ ማውራትን ትተው እንድበረታ በምክራቸው
ይደግፉኝ ነበር" ይላል ሪዮ - ስለዶክመንተሪው ሲናገር።
ሟች ሬቤካ፣ ሊዛ የተባለች ጓደኛ ነበረቻት። ከህልፈቷ በኋላ ሬቤካ ለሊዛ
የተናገረችውን ሪዮ የሰማው ዘግይቶ ነበር። ያቺ መልካም ሴት በሞት አፋፍ ላይ
ሳለች ስለሪዮ የወደፊት ህይወት ምኞቷን ለሊዛ ገልፃላታለች።
"ሪዮ የሌላ ሴት ስለመሆኑ ማሰብ በራሱ ለእኔ ሞት ነው። ነገር ግን ብቸኛ
ስለመሆኑ ማሰብ ደግሞ ይበልጥ የሞት፣ ሞት ይሆንብኛል። ስለዚህ እኔ ከሞትኩ
ከጎኑ የማትለይ አፍቃሪና ደጋፊ ታስፈልገዋለች። ሪዮ በህይወቱ ሁሉ ደስተኛ
እንዲሆን እፈልጋለሁና አፍቃሪ ማግኘት አለበት።"
ዘጋቢ ፊልሙ የባፍታን ሽልማት በማሸነፉ ስሙ ሲጠራ ፈርዲናንድ
ከመቀመጫው በመነሳት ኮቱን ቆልፎ የሳማት ሴት ኬት ራይት ትባላለች። የ27
ዓመቷ የሪያሊቲ ቴሌቪዥን ተዋናይት ተጫዋቹ ሃዘኑን እንዲረሳ ያስቻለችው፣
ሟች ባለቤቱ የተመኘችለት ሴት ሆና ተገኘች። በያዝነው የፈረንጆች ወር
መጀመሪያ በአቡዳቢ፣ ሪዮ ፈርዲናንድ ለሌላ ዘላቂ ህይወት በኬት ራይት ጣት
ላይ የቃልኪዳን ቀለበት አኖረ። ጥንዶቹ ሲተጫጩ ሶስቱም ህፃናት
በአጠገባቸው ቆመው የአባታቸውን ደስታ መመለስ ይመለከቱ ነበር።



ምንጭ - የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ የፌስቡክ ገጽ

No comments:

Post a Comment

"ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል

 "ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል የፈረንሳዊው ኮከብ ፖል ፖግባ ወኪል የሆነው ሚኖ ራዮላ ፤ አማካዩ በክረምት የዝውውር መስኮት ወደ ቱሪን ሊመለ...