Saturday, January 19, 2019

ዲንሆ የማይረሳት ምሽት

ጽሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው

ዲንሆ የማይረሳት ምሽት
!
....ሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ለኤልክላሲኮ በሮቹን ከፈተ። በላ ሊጋው ሰንጠረዥ ላይ
ሪያል ማድሪድ ከባርሴሎና በአንድ ነጥብ ይብለጥ እንጂ በዚያ ሰሞን ነጮቹ
በጉዳትና በብቃት መውረድ ወዛቸው ተሟጦ ተቸግረዋል። ጋላክቲኮስ
እንደስማቸው መሆን አቅቷቸዋል።
ከጨዋታው ቀድሞ ሮናልዲንሆ ውጥረቱን ለማቀዝቀዝ "ሪያል ማድሪድን ማሸነፍ
ሊጉን ማሸነፍ አይደለም። ያው እንደማንኛውም ጨዋታ ሶስት ነጥብ
የምታገኝበት ጨዋታ ነው" በማለት ቀለል ያለ መግለጫ ሰጠ።
ጨዋታው ግን ዲንሆ እንዳቀለለው አልቀለለም። ከጨዋታም በላይ ነበር። ሶስቱ
አጥቂዎች ሳሙኤል ኤቶ፣ ሊዮኔል ሜሲና ሮናልዲንሆ ለባርሴሎና በኃያሉ
ተፎካካሪው ፊት አይበገሬ ግርማ ቸሩት። ኤቶ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጠረ።
ሮናልዲሆ ከጥልቅ ቦታዎች እየተነሳ ጉልበትና የቴክኒክ ልህቀትን አዋህዶ
በሚያስደንቅ አጨራረስ ሁለት ጎሎችን በስሙ አስመዘገበ። ሪያል 0፣ ባርሳ 3።
በዚያች ምሽት ዲንሆ እንደ እንዝርት ሾሮ የባርሴሎናን የብቃት መዘውር
በቴክኒካዊ ብቃቱ አዳወረው። ማድሪዳዊያን በገዛ ጓሯቸው ለማይወዱት
ተፎካካሪያቸው ብርቱ ክንድ እጅ ሰጡ። ሮናልዲንሆና ጓደኞቹ መራራውን የሽንፈት
ፅዋ አስጨለጧቸው። የባርሳ ልጆች ለስህተት ቦታ አልነበራቸውም። ብቃታቸው
ወዳጅን ቀርቶ ባላንጣን የሚያሳምንና ለተሸናፊው ሰበብ የማይመች ነበር። የኑ
ካምፑ ንጉሥ በኃያሉ ፍልሚያ ሜዳ ትልቅነቱን አሳይቶ በቤርናቢዩም ነገሰበት።
ይህ ለሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ከአእምሮ በላይ ሆነባቸው። ከተቀመጡበት
ተነስተው ለመራሩ ባላጋራቸው ተጫዋች አጨበጨቡ።
ጭብጨባው የፍፁማዊ አድናቆት አንጂ የምፀት አልነበረም። ባትወደውም
ከውስጥ የመነጨ የእግር ኳስ መንፈስ የሚያስገድድህ የእውነተኛ ስፖርት
ቤተሰብነት ስሜት ነበር። ከዚያ በፊት ማድሪዲስታስ ለሁለት የባርሳ ተጫዋቾች
ብቻ በአድናቆት አጨብጭበዋል። በፌብርዋሪ 1974 ባርሳ 5-0 ሲረታቸው
ለዮሃን ክራይፍ አድርገውታል። በጁን 1983 የዲዬጎ ማራዶና ብቃት አስገርሞ
ከመቀመጫቸው አስነስቶ አስጨብጭቧቸዋል። በዚያች ምሽት ደግሞ
ሮናልዲንሆ የክራይፍ/ማራዶና የክብር መዝገብ ውስጥ ተካተተ።
"መቼም አልረሳውም። በአንድ ተጫዋች ህይወት ውስጥ እንዲህ አይነቱ ነገር
ከዘመናት አንድ ጊዜ ብቻ የሚያጋጥም ነው" በማለት ሮናልዲንሆ በሪያል
ደጋፊዎች አፀፋ የተሰማውን ደስታ ገለፀ።
ለሪያል ማድሪድ ጋላክቲኮስ የራሳቸው ደጋፊዎች አድናቆታቸውን ነፍገዋቸው፣
ክብራቸውን ለተጋጣሚዎቻቸው ሲሰጡ መመልከት የሚያሳፍር ነበር። ለደካማው
ጥረታቸው ማድሪዳዊያኑ እንዲህ አድርገው ተጫዋቾቻቸውን ቀጧቸው።
በገፅታው አስቀያሚነት ምክንያት ሮናልዲንሆን ማስፈረም "ለሪያል ማድሪድ
ብራንድ ውድቀትን ያስከትላል" ያሉት የቤርናቢዩ ባለስልጣናት በሞኛሞኙ
አስተሳሰባቸው ተጸጸቱበት። ምልመላ በደም ግባት ሳይሆን በጨዋታ ብቃት ብቻ
መሆን እንዳለበት ታሪክ ከክፉ ምክር ጋር አስተማራቸው።
ሽንፈቱ ለቫንደርሌይ ሉክሰምቡርጎ ዘርሮ ከውድድር ውጭ የሚያደርግ ብርቱ
ቡጢ ያህል ነበር። ከዚያ በኋላ የብራዚላዊው አሰልጣኝ የብቃት ቆሌ ተገፎ ቀረ።
አላገገሙም። የሮናልዲንሆ ምትሃት ሪያልን አንገት አስደፍቶ ብቻ አልቀረም።
ብዙም ሳይቆይ ሉክሰምቡርጎ የስንብት ደብዳቤ ደረሳቸው። ጥቂት ወራት ብቻ
እንደተቆጠሩ በፌብርዋሪ 2006 ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ የጋላክቲኮስ ፖሊሲያቸውን
ጥለው በፈቃዳቸው ከፕሬዚዳንትነታቸው ተነሱ።
በዚያ ቤት ለቅሶ ሲሆን በሮናልዲንሆ ዘንድ ደስታው በዛ። 2005 ፍፁም ያማረ
ዘመን ሆኖ ተገባደደለት። ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የፊፋን ኮከብነት ክብር
ተጎናፀፈ። ለመጀመሪያ ጊዜም ባሎን ዶርን አሸነፈ። የወርልድ ሶከር እና የኦንዝ
መፅሔቶችም "አንተ የዓለም ኮከብ ተጫዋች ነህ" ብለው ሸለሙት። ዘመኑም
የሮናልዲንሆ ወርቃማው ዘመን ሆኖ በታሪክ ማህደር ላይ ተፃፈ። እኛ፣ የእግር
ኳስ አፍቃሪዎችም… ማንም ሳይነግረን፣ ከዓለም እግር ኳስ ኃያላን ነገሥታት
ተርታ አሰለፍነው። አልተሳሳትንም ነበር።

No comments:

Post a Comment

"ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል

 "ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል የፈረንሳዊው ኮከብ ፖል ፖግባ ወኪል የሆነው ሚኖ ራዮላ ፤ አማካዩ በክረምት የዝውውር መስኮት ወደ ቱሪን ሊመለ...