ሞሪንሆ አሰልጣኝነታቸውን ከምንጊዜውም በተሻለ አሁን እንደወደዱት ተናገሩ
የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ምንም እንኳን በዚህ ሲዝን ቡድናቸው ስኬታማ መሆን ባይችልም ከምንጊዜውም በተሻለ አሰልጣኝነታቸውን እንደወደዱት ተናገሩ።
ሞሪንሆ ክለባቸው በፕሪሚየር ሊጉ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን አስደናቂ አቋም ላይ የሚገኘውን ሊቨርፑል ነገ ምሽት አንፊልድ ላይ የሚገጥሙም ይሆናል ።
ሆኖም የ55 አመቱ ሰው የመጀመሪያ ሲዝን ግማሹ ላይ ደርሶም ቢሆን አመቱን ዘና እያሉ እና ከምንጊዜውም በተሻለ ስራቸውን እየወደዱ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል ።የስካይ ስፖርቱ ጋዜጣኛ አሁንም ሙያዎትን ይወዱታል? ብሎ ለጠየቃቸው ጥያቄ የሚከተለውን መልሰዋል
"አዎ ከምንጊዜውም በበለጠ።ምክንያቱም ይሄ ከምንጊዜውም በላይ የከበደኝ አመት ነው።አመቱ ከባድ ሊሆንብን እንደሚችልም ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ገምቼ ነበር ።ባሳለፍነው አመት ሁለተኛ ደረጃን ይዘን መጨረሳችን በጣም ትልቅ ውጤት ነበር በዚህም ምክንያት ሰዎች በዚህ አመት የተሻለ ነገርን ይጠብቁ ነበር ፥ከሁለተኛ ደረጃ የተሻለው ደግሞ ሻምፒዮን መሆን ነው።ነገር ግን እኔ ይህ ሊሆን እንደማይችል ተናግሬ ነበር የባለፈው አመት ውጤታችንም በጣም ጥሩ ነበር ።
አሁን ስኬታማ ያልሆንበት ምክንያት ደግሞ ተቀናቃኞቻችን በጣም እየተጠናከሩ እና እየተሻሻሉ መሄዳቸው ነው።"
ብዙዎች ግን ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ሰበብ እየፈለጉ ነው በማለት እየተቿቸው ነው።ጆዜ ሞሪንሆ ዩናይትድን ከያዙ ወዲህ አንፊልድ ላይ ሁለት ጨዋታ አድርገው ሁለቱም 0ለ0 ነበር የተጠናቀቁት።

No comments:
Post a Comment