Sunday, January 20, 2019

ባጅዮ በካሊፎርኒያ ሰማይ ስር

ፅሁፉ የጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው 

Moments:
ባጅዮ በካሊፎርኒያ ሰማይ ስር
…በመልበሻ ቤት ውስጥ ከቡድን ጓደኞቹ ተነጥሎ ተቀመጠ። እንደፈረስ ጭራ
ወደ ኋላ የተዘረጋው ፀጉሩ ጀርባው ላይ እንደተጋደመ፣ ጭንቅላቱን በእጆቹ
መዳፎች ላይ አሳርፎ በዝምታ ቆየ። ጓደኞቹ ምን እያደረገ እንደሆነ
አልገባቸውም። ጭንቀት ይሆን? ወይስ ፀሎት እያደረሰ ነው? እርግጠኛ መልስ
ያለው አልነበረም።
ከ1994ቱ የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ በኋላ ነበር። ሮቤርቶ ባጅዮ ቡልጋሪያ
ላይ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ሃገሩን ለፍፃሜ ቢያደርሳትም እንደ ድል ነሺ ሳተና
በኩራት አልተኮፈሰም። በውድድሩ ያስቆጠራቸው አምስት ጎሎች የአሪጎ ሳኪን
ቡድን ለዋንጫው ሽሚያ ያድርሰው እንጂ የባጅዮ ደስታ ሞልቶ አልፈሰሰም።
ጎዶሎ ነው። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ የደረሰበት ጉዳት በፍፃሜው ፍልሚያ
ላይ ተሳታፊ ይሁን ወይም አይሁን እርግጠኛ እንዳይሆን ሳንካ ፈጠረበት።
ያለመሰለፍ ዕድሉ ሰፊ ሆነ።
በካቶሊካዊት ክርስትና እምነት ተከታዮች የተሞላው መልበሻ ቤት 10 ቁጥራቸው
ፀሎት እያደረገ ስለመሆኑ ማወቅ አይችልም። ገና ከአፍላነት ዕድሜው ጀምሮ
የቡድሂዝም ተከታይ ሆኗልና የፀሎት ስርዓቱ ከክርስትናው ጋር ለየቅል ነው።
ማቀርቀሩ ፀሎት ይሁን ብስጭት ጓደኞቹ ያላወቁት ለዚህ ነበር።
የባጅዮ ድርጊት ፀሎትም ይሁን ጭንቀት የሃሳቡ ማዕከል የፍፃሜው ጨዋታ
ነው። ጉዳትና የተጫዋቾች ቅጣት ያሳሰባት የባጅዮ ጣልያን ከብራዚል ጋር
ትጫወታለች። በካሳዴና፣ ካሊፎርኒያ፣ ሮዝ ቦውል ስታዲየም፣ ጁላይ 17 ቀን
1994።
… ቡልጋሪያን ያሸነፉት በኒውዮርክ ነበር። ፍፃሜው በሩቁ ካሊፎርኒያ ግዛት
መሆኑ ጣልያናዊያኑን አላስደሰተም። የስድስት ሰዓት የአውሮፕን ጉዞ ማድረግ
ግዴታቸው ሆነ። የብራዚል ቡድን ደግሞ ግማሽ ፍፃሜውን ያከናወነው እዚያው
ነው። የጉዞ ድካም የለበትም። ባጅዮ ደግሞ ከጉዞ ድካምም ባለፈ የጭን ጅማት
መሳሳብ አሳስቦታል።
በአንድ የባንግላዴሽ የቡድሂዝም ቤተመቅደስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡድሃ
መነኮሳት ባጅዮ ብቁ ሆኖ ሜዳ እንዲገባ የህብረት ፀሎት አደረጉለት። ከዓለም
ዋንጫው በፊት መነኮሳቱ ጣልያን ድረስ ተጉዘው ባጅዮን በጎበኙበት ጊዜ ፀሎቱ
የተደረገበት ቤተመቅደስ የሚታደስበትን ወጪ ሸፍኖላቸው ነበር።
ሁለት የማገገሚያ ቀናትን ብቻ ቢያሳልፍም የባጅዮ ጭን በወፍራም ፋሻ
ተጠቅልሎ ብራዚልን ሊፋለም ገባ።
መደበኛውም ሆነ ጭማሪው ሰዓት አሸናፊውን መለየት አላስቻለም። መለያ ምት
ግድ ሆነ።
ብራዚላዊያን የዓለም ሻምፒዮን መባል ናፍቋቸዋል። ክብሩን ካገኙ 24 ዓመታት
ተቆጥረዋል። አዲሱ ትውልድ በአባቶቹ ሲነገረው የኖረውን የድል ታሪክ ሊኖረው
ቋምጧል። ጣልያን ደግሞ በዚህ ትውልድ ህልም መንገድ ላይ ቆማለች።
ወቅቱ ለጣልያን እግር ኳስ የኃያልነት ዘመን ነበር። የዓለማችን ሶስቱ ውድ
ተጫዋቾች የሚጫወቱት በሴሪ አ ነው። ጂያንሉዊጂ ሌንቲኒ፣ ዣን ፒየር ፓፐ እና
ጂያንሉካ ቪያሊ። በ1994 ቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ የፋቢዮ ካፔሎ ኤሲ ሚላን
የዮሃን ክራይፍን ባርሴሎና 4-0 ረምርሞ አውሮፓዊ ዘውዱን ደፍቷል። እናም
ጣልያን ለብራዚል ከባድ ተጋጣሚ ነበረች።
…ባጅዮ ወሳኟን መለያ ምት ሊመታ መጣ። ኳሷን በነጥቧ ላይ አስቀመጠ።
የባጅዮ ኳስ ካልተቆጠረች ከእነፔሌ ዘመን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚል
የወርቁን ዋንጫ ይዛ ሃገሯ ትገባለች።
ሲንደረደር ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥኑ ወጣ። በእርጋታ ሊመታት ተዘጋጀ።
የብራዚል በረኛ ክላውዲዮ ታፋሬል በፍፁም ቅጣት ምት መሳሳትን ከማያውቅ
ኮከብ ጋር ተጋፈጠ። 94ሺህ ተመልካች በሮዝ ቦውል የመጨረሻዋን ቅፅበት
ሊመለከት አይኑን ባጅዮ ላይ ተከለ።
ሮጥ ብሎ ኳሷን መታት። ታፋሬል ወደ ግራው ለመውደቅ ቢሞክርም የባጅዮ ኳስ
ከግቡ አግዳሚ ርቃ ወደ ላይ በረረች። ብራዚላዊያን በድል መንፈስ ሲዋጡ
የጣልያናዊያን ተስፋ የማይገፈፍ ድቅድቅ ጨለማ ወረሰው። በስታዲየሙ
ብራዚላዊያን የድል ብስራቱን በጭፈራ አደመቁት። የሳኪ ልጆች ግን መንፈሳቸው
ተሰበረ። ባጅዮ ሁለት እጆቹን በሽንጡ ላይ እንዳሳረፈ ቆሞ አቀረቀረ።
ሮቢ መወደድን፣ መጠላትን፣ መደነቅን፣ መተቸትን፣ ልይህ ልይህ፣ አይንህን ላፈር
መባልን ያውቀዋል። ከፊዮሬንቲና ወደ ጁቬንትስ በዓለም ሪከርድ ዋጋ ሲዛወር
በፍሎረንስ ከተማ የጎዳና ላይ አመፅ ተቀስቅሶ ነበር። በወቅቱ የ1990 የዓለም
ዋንጫ ተቃርቦ ስለነበር አዙሪ በፍሎረንስ አቅራቢያ በሚገኘው ኮቬርቺያኖ
ማዕከል መዘጋጀት እንኳን አልቻለም። በአመፁ ምክንያት የዝግጅት ቦታውን
ለመቀየር ተገደደ። በ"ወይንጠጆቹ" ደጋፊዎች የተወደደውን ያህል ተጠላ።
በአሜሪካኑ የዓለም ዋንጫ ዘግይቶ ስኬቱን ቢጀምርም በአምስቱ ጎሎች መሬት
አይንካህ ተብሎ ሳለ፣ በፍፃሜው መለያ ምቱን ባለማስቆጠሩ ብቻ ገሸሽ
ተደረገ።
ባጅዮ የዓለም ዋንጫን አሳይቶ ከነሳት በኋላ ጣልያን ሃዘን ገባት። ከሽንፈቱ በኋላ
ምሽቱን ተጫዋቾች በጋራ ሊመገቡ ከየሆቴል ክፍላቸው ሲወጡ ሮቤርቶ ባጅዮ
አልተቀላቀላቸውም። በራሱ ክፍል ላይ ቆልፎ ብቻውን ተቀመጠ። ረጅሙን
የቁዘማ ጉዞም አጥብቆ ተያያዘው።
በቻርተር በረራ ሮም ሲደርሱ ባጅዮ በደበዘዘ ስሜት ከአውሮፕላኑ ወጣ።
"አየሩን ስስብ የጣልያንን ህዝብ ሃዘን በአፍንጫዬ ያስገባሁ ያህል ተሰማኝ"
በማለት ከአሜሪካ ይዞት የመጣው ጫና የሃገሩን ምድር ሲረግጥ
እንደተባባሰበት ተናገረ።
ከአንድ ወር በላይ ድብርቱ ተጫነው። እንቅልፉ ተዛባ። የውስጥ ሰላሙ ታወከ።
የጥፋተኛነቱ ስሜት ጎዳው። ከዚያም በኋላ ባጅዮ የቀድሞው ባጅዮን አልሆነም።
ከአንድ ዓመት በኋላ ማርቼሎ ሊፒ ለሚላን ሸጡት። በሚላን ብቃቱ አላመረቃም።
ቦሎኛ፣ ኢንተር፣ ብሬሺያ ተዟዙሮ ተጫወተ። ከኃያላኑ ይልቅ አነስ ባሉት ክለቦች
ውስጥ የተሻለ ተጫወተ።
በ2004 ከተጫዋችነት ዓለም ከተለየ በኋላ ባሎን ዶር የተሸለመበት ብቃቱ
ሳይሆን በጁላይ 17ቷ መለያ ምት ስህተቱ ይበልጥ ይታወስ ያዘ። እስከዚያች
ዕድለ ቢስ ዕለት ድረስ ፍፁም ቅጣት ምት ከባጅዮ ብዙ ጠንካራ ጎኖች አንዱ
ነበር። እጅግ በጣም አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት ግን ጥንካሬው ከዳው። ቀን
ሲጥል ደግሞ ሰው ብቻ አይደለም፣ የገዛ ህሊናም አፅናኝ አይሆን!
ሮም ከደረሱ በኋላ ሳኪ ባጅዮን ተመለከቱት። አዩት፣ አያቸው። ከፍፃሜው ጨዋታ
በፊት ባሉት ቀናት ተጫዋቾቻቸውን ደጋግመው የጠየቁትን ጥያቄ ደገሙለት።
"ሮቢ እስቲ ወደ ላይ ተመልከት"
ባጅዮ ወደ ሰማዩ አየ።
"ከሰሞኑ የተለየ ነገር ይታይሃል?"
የ24 ዓመቱ ኮከብ ምንም የተለየ ነገር አላገኘም።
"በቃ! ይኸው ነው!" አሉት።
እውነት ነው! የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ላይ ወሳኟን መለያ ብትስትም፣ ሃገርህ
የዓለም ሻምፒዮን እንዳትሆን ያደረግከው አንተ ብትሆንም፣ የሃገርህን ዜጎች
ሃዘን ላይ ብትጥልም፣ ጀግንነትህ በአንዲት ምት ብቻ በጥፋተኝነት ቢቀየርም፣
የዓለም ፍፃሜ አይደለም። ህይወት ትቀጥላለች።

No comments:

Post a Comment

"ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል

 "ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል የፈረንሳዊው ኮከብ ፖል ፖግባ ወኪል የሆነው ሚኖ ራዮላ ፤ አማካዩ በክረምት የዝውውር መስኮት ወደ ቱሪን ሊመለ...