Wednesday, January 9, 2019

ኢኒዬሽታ፣ ያርኬና የዓለም ዋንጫ

ጸሀፊው ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው

Moments:
ኢኒዬሽታ፣ ያርኬና የዓለም ዋንጫ
ጎሉ ሊቆጠር እንደሆነ ልቦናዋ አውቋል። አይኗን በሁለት እጆቿ ሸፍና በጨለማ
ውስጥ ተደበቀች። ሆድ ባሳት። እያመነታች እጆቿን ገለጥ አድርጋ ወደ ቴሌቪዥኑ
ተመለከተች። እንደገና ወደ ጨለማው ገባች። ደግማ የእጆቿን መጋረጃ ገለጥ
አድርጋ አየች። አንድሬስ ኢኒዬሽታ ጎሉን አስቆጥሮ ይሮጣል። …ከዚያ በኋላ
ያልጠበቀችው ሆነ። አይኖቿን ማመን አቃታት። መላዋ ስፔን በደስታ ስካር
ስታብድ፣ እርሷ ተንሰቅስቃ አለቀሰች።
ጄሲካ ያርኬ እግር ኳስ ጨዋታን በቴሌቪዥን ከተመለከተች አንድ ዓመት
ደፍናለች። የህይወቷ ግማሽ አካል ሴት ልጁን ብቻ ለስም መጠሪያ ጥሎላት
ላይመለስ ሄዷል። ዳኒ ምን አይነት ሰው መሰላችሁ? የመልካም ሰው ልክ፣
አሳቢ፣ አፍቃሪና ተንከባካቢ ፍቅሯ ነበር።
ጄሲ ፉትቦልን ለፍቅረኛዋ ብላ ትመልከት እንጂ ጥሩና መጥፎ ጨዋታን እንኳን
መለየት አትችልም። ዳኒ ደግሞ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ነው። ከከተማ ውጭ
ጨዋታ ካለበት የባለቤቷን ጨዋታ፣ ለእርሱ ብላ በቴሌቪዥን መመልከቷ
የማይቀር ነበር። ከጨዋታ መልስ ማታ ቤት ሲገባ በግጥሚያው ላይ ስላሳየው
ብቃት ይጠይቃታል።
"ውዴ! ዛሬ ጨዋታዬን እንዴት አየሽው?"
ጥቂት አሰብ እያደረገች… "ዛሬ ብቃትህ ልዩ ነበር" ትለዋለች። ዳኒ ተሰጥኦውን
ባላሳየበት ጨዋታ ላይ የጄሲካ መልስ እንዲህ ነበር። ተቃራኒውን የተጠየቀች
ይመስል ድፍን ስታዲየም ካደነቀው በኋላ "ጥሩ አልተጫወትክም" ማለቷን
ለምዶታል።
እርሱም አይፈርድባትም፣ ይ'ረዳታል። እርሱን ማፍቀሯ ይበቃዋል። የዕለቱ
ውሎውና የባለቤቱ መልስ አራምባና ቆቦ መሆኑን ለምዶታል።
…በዚያ እርጉም ነሐሴ ዳኒ ከኤስፓንዮል ጋር ለቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት
ወደ ጣልያን አመራ። በወሩ በስምንተኛ ቀን ጠዋቱን በልምምድ አሳለፈ።
አመሻሹ ላይ በኮቬርቺያኖ በመኝታ ክፍሉ ገብቶ ከነፍሰ ጡሯ ፍቅረኛው ጋር
ስልክ እያወራ ሳለ ተዝለፍልፎ ወደቀ። የጤና ባለሙያዎች ከሞት ሊታደጉት
ተረባረቡለት። ለአንድ ሰዓት ልቡን ወደ መደበኛ ስራ ለማስገባት የተደረገው
ጥረት ሁሉ ያለ ፍሬ አብቅቶ ዳኒ በ26 ዓመቱ ይህን ዓለም ተሰናበተ።
ኤስፓንዮል ወደ ሃገሩ ሲመለስ፣ ጄሲካ እንደ ወትሮው ምሽቱን ስለማታውቀው
እግር ኳስ የሚጠይቃትን የህይወቷን ፍቅር በኤርፖርት አልተቀበለችውም።
ድምፁ በድንገት ተቋርጦ፣ ትንፋሽ አጥሮትና የሚናገርበትን አቅም አጥቶ
አልተሰናበታትም።
መጥፎውን ዜና ከሰማችባት ከዚያች ዕለት ወዲህ እግር ኳስን ማየት እርም
አለች። በቲቪ መስኮት ፊት ሳትቀመጥ አንድ ዓመት አለፈ። የአባትን ጣዕም
የማታውቀው የአንድ ዓመት ህጻን ልጇ እንኳን በቴሌቪዥን ጨዋታ
እንድትመለከት የእናት ፍላጎት አይደለም። እግር ኳስ የውስጥ እግር እሣት
ሆኖባት ቀረ።
አባቷን ለአንድ ቀን እንኳን ለማየት ያልታደለችው ማርቲና በዚያ ጨቅላ ዕድሜዋ
ለይታ የምታውቀው አንድ እግር ኳስ ተጫዋች አለ። የኢኒዬሽታን የማስታወቂያ
ምስል በባርሴሎና ከተማ ቢልቦርዶች ላይ ያየች እንደሆነ በብሩህ ፈገግታ
"እማዬ እዪው" እያለች ጣቷን ወደ ፖስተሩ መጠቆሟን ጄሲካ ለምዳዋለች።
ኢኒዬሽታና ያርኬ የልጅነት ጓደኛሞች ናቸው። አንድሬስ ለዳኒ ጓዳ ቤተኛ ነው።
ለጄሲካም ቅርብ ነው። በኋላም ማርቲናም ተላምዳዋለች። ባርሳ ከኤስፓንዮል
ጋር ከተጫወተ ማሊያ ይቀያየራሉ። የኢኒዬሽታን ማሊያ የሚፈልጉ ዳኒ ቤት
መጥተው ሳያገኙ አይሄዱም። ለጋሱ ዳኒም ይሰጣቸዋል።
ሁለቱ የልጅነት ጓደኞች በአንድ ከተማ ኖረዋል። ለስፔን ወጣት ብሔራዊ ቡድን
አብረው ተጫውተዋል። ከውጭ ሃገር ጉዞ ሲመለሱ፣ አንድሬስ መኪና
ስላልነበረው ዳኒ ከኤርፖርት ወደ ቤት ያደርሰዋል። ኢንዬሽታም ሌላ መኪና
አይፈልግም። "ታክሲ ሹፌር ሆኖልኝ ነበር" እያለ ይቀልድበት ነበር። ዳኒ የአንድ
ዓመት ታላቁ ነው። ፉትቦል ይበልጥ አቀራርቦ አንድ አካል አድርጓቸዋል።
የዳኒ ድንገተኛ ህልፈት ለኢኒዬሽታም ሞት ሆነ። ለጄሲ ደግሞ የሞት፣ ሞት።
ሁለቱም አንድ ጎናቸው ተገንጥሎ የወደቀ ያህል መንፈሳቸው ታወከ። ከአንጀት
በማይወጣ ሃዘን አረሩ።
ኢኒዬሽታ ባርሳን ተሰናብቶ ወደ ጃፓን ባመራ ጊዜ "…ከያርኬ ሞት በኋላ ውስጤ
ሞተ። ለሁሉ ነገር የነበረኝ ፍላጎት ቀዘቀዘ። ጉጉቴ ሁሉ ከውስጤ ተነነ…" በማለት
የልቡን ቁስል ለጋዜጠኞች ገልጦ አሳይቷል።
ሁሉ ከንቱ የሆነባት ጄሲካም ከእግር ኳስ ተመልካችነት ሸሸች። በቴሌቪዥም
ቢሆን እንኳን ላታየው ቆረጠች።
ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ስፔን ለ2010 የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ስትደርስ ግን
አላስቻላትም። ጄሲ በቴሌቪዥኑ ፊት ስትቀመጥ ያለፉትን 12 ወራት እንዴት
እንዳሳለፈች የሚያውቁት እናቷ ማመን አቅቷቸው በአንክሮ ተመለከቷት።
"እርግጠኛ ነሽ? እውን ጨዋታውን ትመለከቻለሽ?"
"አዎ እማዬ፣ ዛሬስ አያለሁ።"
ሆድ እንደሚብሳት ያውቃሉና እናት ማረጋገጫ መፈለጋቸው አያስገርምም።
ባለቤቷ በህይወት እያለ ይወድ እንደነበረው በሰዎች ተከባም ቢሆን ጨዋታውን
ለመመልከት መወሰኗ ከልብ ነበር።
ጨዋታው በ0-0 ውጤት ቀጥሎ፣ በጭማሪው ሰዓት አራተኛ ደቂቃ ላይ፣
ኢኒዬሽታ ወደ ጎሉ ተጠጋ።
"አንድ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ውስጤ ይነግረኝ ነበር…" ጄሲካ ያቺን ሰዓት
ታስታውሳለች።
"እንግዳ ስሜት ተሰማኝ።… እንዴት እንደሆነ ባላውቅም…፣ ዳኒ በዚያ ጨዋታ
ላይ እንደሚገኝ አምኜ ነበር። በዚያች ቅፅበት ጎሉ እንደሚቆጠርም ተረዳሁ።
"እናቴ 'ኧረ እዪው! እዪው! እዪው!…' ብላ ጮኸች።
"ማየት አይበለው!… አይኖቼን በእጆቼ እየሸፈንኩና እየገለጥኩ አየሁት።
በመጨረሻ ጨከን ብዬ ሳተኩር ኢኒዬሽታ ጎል አስቆጥሮ ሲሮጥ ተመለከትኩት።
ዕይታዬን ሳጠራ የለበሰው የስፔን ማሊያ በላዩ ላይ የለም።"
አንድ ዓረፍተ ነገር እንኳን ሳታቋርጥ ትዝታዋን መናገር አልቻለችም። ሳግ
በቆራረጠው ድምፅ ቀጠለች።
"ስፔንን ለዓለም ሻምፒዮንነት ያበቃችውን ብቸኛ ጎል ለባለቤቱ፣ ለልጆቹ ወይም
ለሌላ ማስታወሻነት ማበርከት ይችል ነበር። ኢኒዬሽታ ግን እንዲህ ነው…።"
አንድሬስ ኢንዬሽታ ማሊያውን አውልቆ ከውስጥ በለበሰው ነጭ ካኒቴራ ላይ
በማርከር የተፃፈውን መልዕክት ለዓለም አሳየ።
"Dani Jarque, siempre con nosotros" ይላል።
"ዳኒ ያርኬ፣ ምንጊዜም ከእኛ ጋር ነህ!"

No comments:

Post a Comment

"ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል

 "ቱሪን አሁንም በልቡ ውስጥ አለ" ራዮላ ፖግባ ወደ ዩቬንትስ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል የፈረንሳዊው ኮከብ ፖል ፖግባ ወኪል የሆነው ሚኖ ራዮላ ፤ አማካዩ በክረምት የዝውውር መስኮት ወደ ቱሪን ሊመለ...